"ኦሮማይ!… እንደገና! ጦርነት ይብቃ፣ ሰላም ይምጣ!"-በአቶ ልደቱ አያሌው ለመሠረት ሚድያ የተላከ
1. እንደ መግቢያ፣ እየተላለቅን መፍረስ- ለምን?
የብልፅግና አገዛዝ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በተለያዩ ወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች ዙሪያ ለንባብ ያበቃኋቸው በርካታ ፅሁፎቸ ተነበዋል፣ በተለያዩ መገናኛ-ብዙሀን ያካሄድኳቸው ውይይቶችና ቃለ-ምልልሶች በስፋት ተደምጠዋል። የእነዚህ ጽሁፎቸ እና ቃለ-ምልልሶቸ አብዛኛው የመዝጊያ መልዕክት- “አሁን በያዝነው መንገድ ከቀጠልን እየተላለቅን እንፈርሳለን” የሚል ነበር። ይህንን የምለው፣ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ጨለምተኛ ወይም ሟርተኛ ሰው ስለሆንኩ አይደለም። እንደ አንድ ሙሉ ዕድሜውን በትግል ውስጥ እንዳሳለፈና የሙሉ ጊዜ ፖለቲከኛ እንደሆነ ሰው የምለውን እያልሁ ያለሁት በስሜት ሳይሆን በተጨባጭ ምክኒያት ነው።
በምክኒያት እንደሆነም ቅንነትና አስተውሎት ላለው ሰው ሁሉ እምብዛም የተሰወረ አይመስለኝም። ለዚህ አባባሌ፣ ከአሁን ቀደም በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያቀረብኳቸው ግምገማዎች ከበቂ በላይ የሆነ እማኝነትን ያሳዩ ይመስለኛል። በእርግጥም አስካሁን “እየተላለቅን እንፈርሳለን” ስል የነበረው ያለ ምክኒያት ሳይሆን -
ኢትዮዽያውያን ከመቸውም ጊዜ በላይ የአንድ ሀገር ልጅነት ትስስራችን እየተበጣጠሰ መምጣቱን፤
የፖለቲካ ዕውቀት ማለት አካታችና አስተባባሪ መፍትሄን ማፍለቅ ሳይሆን አክራሪ የብሄርተኝነትና የጦረኝነት አጀንዳ ማራመድ እየሆነ መምጣቱን፤
ከትህትናና ከርህራሄ ይልቅ ጥላቻና ጭካኔ የትውልዱ ዋና መገለጫ ባህሪ እየሆነ መምጣቱን፤
ሀገርን፣ አንድነትንና ሰላምን መውደድ የኋላ-ቀርነትና የአላዋቂነት መገለጫ እየሆነ መምጣቱን፤
ፖለቲካ ዕውቀትንና ልምድን የሚጠይቅ ክህሎት ሳይሆን የጀብደኞች፣ የጥላቻ አራማጆችና የአሉባልተኞች ዋና ተግባር እየሆነ መምጣቱን፤
የሁላችንም የጋራ ጨቋኝ የሆነውን አገዛዝ በጋራ ከመታገል ይልቅ የጐንዮሽ ቅራኔና ትግል የበለጠ ቦታ እያገኘ መምጣቱን፤
ሀላፊነትና ተጠያቂነት ጠፍቶ በህዝብ ፍጅትና ዕልቂት ጭምር ስልጣንን መያዝም ሆነ ማፅናት የሚያኮራ ተግባር እየሆነ መምጣቱን፤
በስልጣን ላይ ያለው አገዛዝ ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ኃይሎችና ዜጐች ጭምር የሀገሪቱን እየተላለቁ የመፍረስ አደጋ የበለጠ ፈጣንና አይቀሬ ለማድረግ ተግተን እየሰራን መሆኑን፤
በአጠቃላይ- እንደ መንግስት፣ ተቃዋሚ ኃይልና ህዝብ የፖለቲካ አስተሳሰብ ብቃታችን ከመዳበር ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ እየቀነጨረ መምጣቱን በውል ስለምገነዘብ ነበር።
ከእዚህ የእኔ ግምገማ በተቃራኒ “ግዴለህም አትስጋ፣ ኢትዮዽያችን አትፈርስም” የሚሉኝና እነሱን መሆን የሚያስቀኑኝ በጐ አሳቢዎች ብዙዎች ናቸው። የሁልጊዜ ምኞቴም የእኔ ስጋት ስህተት ሆኖ የእነሱ ምኞት ዕውን እንዲሆን ነው። ይሁንና ለዚህ “ለኢትዮዽያችን አትፈርስም” ብያኔ ኃይማኖታዊ ትርጉም ለመስጠት ከመሞከር ባለፈ በፖለቲካዊ አመክንዮ ተከራክሮ ሊያሳምነኝ የሞከረ ሰው እስካሁን አጋጥሞኝ አያውቅም።
እርግጥ ነው ደራሲ በዓሉ ግርማ በኦሮማይ መፅሀፉ፣ እነ ጀነራል ፋንታ በላይ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራቸው ለዚያ ትውልድ ከፊቱ እየመጣ ያለውን አደጋ በነብሳቸው ተወራርደው ሊነግሩት ቢሞክሩም አውጋዥና ተሳላቂ እንጂ አድማጭ አላገኙም ነበር። መጨረሻም ላይ ህይዎታቸውን ያጡበት ስጋታቸው ዕውን ሆነ እንጂ በከፈሉት የህይዎት ዋጋ በሀገርና በህዝብ ላይ ከመሆን ያስቀሩት ምንም ዓይነት አደጋ አልነበረም። ዛሬ ላይ እኔንም እያብሰከሰከኝ ያለው ብሶትና ስጋት ትናንት በእነሱ ልቦና ውስጥ የነበረው የተስፋ መቁረጥ ስሜትና ሰሚ የማጣት ቁጭት እንደሆነ ይሰማኛል።
በእርግጥም እኛ ሁል ጊዜም ከተደጋጋሚ ውድቀታችንና መከራችን የማንማር፣ ታሪክም ራሱን እየደገመ ብቻ ሳይሆን እየደጋገመ እንደቀጠለ እየታዘቡ እንደ መኖር አብዝቶ የሚያም ቁጭትና ጸጸት የለም።
ዛሬ ላይ ባለኝ መረዳት፣ “የሰይጣን ጆሮ አይስማኝና” እየተላለቅን የመፈራረሱ አደጋ የመጨረሻው መጨረሻ ላይ እየደረሰ ነው ባይ ነኝ። እየተላለቁ መፈራረስን እውን ሊያደርግ የሚችል ሌላ ዙር አውዳሚ ጦርነት ከፊታችን አፍጥጦ እየመጣ ነውና—። በአንድ በኩል፣ በቀይ-ባህርና አካባቢው ጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅም አለን ብለው ከሚያምኑ የውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር የብልፅግና አገዛዝ በኤርትራና በተባባሪዎቿ ላይ ከተሳሳተ ስሌት የመነጨ አደገኛ ጦርነት ለመክፈት ሁለንተናዊ ዝግጅቱን እየጨረሰ ይመስላል። ከማገዶ እንጨት የተሻለ ዋጋ የማይሰጣቸው የሀገራችን ባተሌ ወጣቶች ወደ ሙታን ማሰልጠኛ በገፍ እየታፈሱ በመጋዝ ላይ ናቸው። በሌላ በኩል- ህወሀትን፣ የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትንና ፋኖን (በከፊ) የመሳሰሉት ታጣቂ ኃይሎች ምን የጋራ አጀንዳ እንደቀመሩልን በግልፅ ባይነገሩንም “የጠላቴ ጠላት ወዳጀ” በሚለው የተለመደ ዕሳቤ ተባብረውና ከሻዕቢያ ጋር ጭምር ተጣምረው በብልፅግናው አገዛዝ ላይ ለመዝመት እየተዘጋጁ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር እየሆነ ነው።
ይህን ዓይነት አዲስ የኃይል አሰላለፍ የያዘ ተጨማሪ ጦርነት ለይቶለት በአካባቢው ከፈነዳ ውጤቱ በሀገራችን መንግስት-የለሽ ሁኔታን ከመፍጠርም ባለፈ እንደ ሀገርና ህዝብ እየተላለቁ የመፈራረስን አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል መገመት አስቸጋሪ አይመስለኝም።
“በቀይ-ባህርና አካባቢው ጂኦ-ፖለቲካዊ ጥቅም አለን ብለው ከሚያምኑ የውጭ ኃይሎች ጋር በመተባበር የብልፅግና አገዛዝ በኤርትራና በተባባሪዎቿ ላይ ከተሳሳተ ስሌት የመነጨ አደገኛ ጦርነት ለመክፈት ሁለንተናዊ ዝግጅቱን እየጨረሰ ይመስላል”
የዚህ ጦርነት ውጤት እንኳንስ ኢትዮዽያን ምስራቅ አፍሪካን ወደ አጠቃላይ ቀውስና ትርምስ የመምራት ዕድሉ ሰፊ ነው። በዚህ ደረጃ እየመጣ ያለውን አደጋ ምክኒያት የለሽ በሆነ አምልኮትና በበጐ ምኞት ብቻ ማስቀረት የሚቻል አይመስለኝም። ይልቁንም ገዥው ፓርቲ፣ ተቃዋሚ ኃይሎች፣ የኢትዮዽያ ህዝብ፣ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮዽያዊያን፣ የኤርትራ መንግስትና ህዝብ፣ ምዕራባዊያንና ዓለም-አቀፍ ተቋማት ጦርነቱን ሊያስቀር የሚችል የየበኩላቸውን ተጨባጭና ደፋር እርምጃዎች መውሰድ ይጠበቅባቸዋል።
2. ከማን ምን ይጠበቃል?
2.1. ከኢትዮዽያ መንግስት
ይህንን ከፊታችን አፍጥጦ እየመጣ ያለ አውዳሚ ጦርነት ለማስቀረት ከማንም በላይ ሰፊ ዕድል ያለው የብልፅግና አገዛዝ ነው። አገዛዙ ለህዝብና ለሀገር ደህንነት ማሰብ ቢሳነው እንኳ ቢያንስ ለራሱና ለቤተሰቦቹ ደህንነት ሲል ጦርነቱ እንዳይነሳ ማድረግ አለበት። ጦርነቱን ከልቡ ማስቀረት ከፈለገም- በባህር-በር ጥያቄ ሰበብ የኤርትራን ሉዓላዊነት ለመጣስና አሰብን ለመውረር፣ ፋኖንና የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊትን በጦርነት አሸንፎ ለማጥፋት፣ ህወሀትን እንደገና በአሸባሪነት ለመፈረጅና ከፖለቲካ ድርጅትነት ለመፋቅ፣ ሰላማዊ ፓርቲዎችን በአፈና በማዳከም የአገዛዝ ስልጣኑን ለዘመናት ለማፅናት የሚያደርገውን ሙከራ ሁሉ እርግፍ አድርጐ መተው አለበት። በምትኩም ከታጣቂ ኃይሎች ጋር ሀቀኛ የተኩስ ማቆም ስምምነት ለመፈራረምና ሁሉን-ዓቀፍ የሆነ አዲስ የሽግግር ሂደት በሀገሪቱ ለመጀመር መወሰን አለበት። ላለፉት ሰባት ዓመታት ከበቂ በላይ እንደታዘብነው ከዚህ ባነሰ ሌላ ጥገናዊ መፍትሄ ጦርነትን ማስቆምና የራስንም ሆነ የሀገርን ህልውና ከጥፋት መታደግ ከቶውንም አይቻልም። ትርፉ አጉል መላላጥ ብቻ ነው።
2.2. ከተቃዋሚው ጐራ
አገዛዙ ከላይ የተጠቀሰውን መፍትሄ በበጐ ፈቃድ መቀበል እንደማይፈልግ አስቀድሞ የታዎቀ ነው። አገዛዙ እስከ መጨረሻው ድረስ አጥፍቶን ሊጠፋ በትጋት እየሰራ ነው። በዚህም ምክኒያት እየተላለቁ ከመፍረስ የመዳኑ መፍትሄ ከእንግዲህ በዋናነት የሚጠበቀው ከአገዛዙ ሳይሆን ከተቃዋሚው ጐራና ከህዝቡ መሆኑ የግድ ይሆናል።
ተቃዋሚው ጐራ በውስጣዊ የስልጣን ሽኩቻ ከመራኮት ይልቅ ውስጣዊ አንድነቱን ጠብቆ በጠንካራ ድርጅት ከተመራ፣ በልዩነት አጀንዳ ላይ ከማተኮር ይልቅ ለጋራ ሀገራዊ ጉዳዮች የበለጠ ትኩረት ከሰጠና የጐንዮሽ የእርስ-በዕርስ ቅራኔዎችን አርግቦ ዋና ትኩረቱን በስልጣን ላይ ባለው አገዛዝ ላይ ካደረገ፣ ሰላማዊ ትግል ከማንኛውም የትግል ስልት በላይ ኃያል አቅም መሆኑን አምኖ ከተቀበለ በስልጣን ላይ ያለውን አገዛዝ በቀላሉ ለእውነተኛ ድርድር ሊያንበረክከው ወይም በህዝብ ትግል ሊያሸንፈው ይችላል። ስለሆነም ተቃዋሚ ፓርቲዎች “ጦርነት ይብቃ! ሰላም ይምጣ!” የሚለውን ወቅታዊና አንገብጋቢ አጀንዳ በማንገብ መንግስት በህዝብ ትግል ተገዶ ሀቀኛና ዘላቂ የተኩስ ማቆም ስምምነት እንዲፈርም፣ ከዚያም ሁሉን-አቀፍና አዲስ የሽግግር ሂደት እንዲጀመር የሚያስችል ”አገዛዝ አንቀጥቅጥ” የሆነ ጠንካራና የተባበረ ትግል ማካሄድ አለባቸው።
በእኔ ዕይታ፣ የሚሰራውን በአግባቡ በማዎቅ የበቃና የሚጠበቅበትን መስዋዕትነት በፅናት ለመክፈል የተዘጋጀ ተቃዋሚ ኃይል በሀገሪቱ ቢኖር ኖሮ የወቅቱን አገዛዝ ለማሸነፍ በተጋነነ ግምት ከሶስት ወራት የበለጠ ጊዜ ባልጠየቀን ነበር። የሚያሳዝነው ተቃዋሚዎች ሁለንተናዊ ብቃት ለመፍጠር ይቅርና ተከባብሮ ለመነጋገርና ለመግባባት እንኳንስ ሶስት ወራት ሌላ ሶስት አስርት ዓመታትም የሚበቃን አንመስልም። የኛ መረን ያጣ ድክመት እስካልተፈታ ድረስም፣ የቱንም ያህል ደካማና በህዝብ የተጠላ ቢሆንም ተላልቀን እስከምንፈርስ ድረስ አገዛዙ በስልጣን ላይ መቆየቱ አይቀርም።
2.3. ከኢትዮዽያ ህዝብ
“እንዳለመታደል” ሆነና ሀገሪቱ የምትፈልገውን መፍትሄ ለማምጣት ገዥው ፓርቲ ፍላጐቱ፣ ተቃዋሚው ጐራ ደግሞ ብቃቱ የለውም። እነዚህ ሁለት ኃይሎች እየተላለቁ ከመፍረስ ሊታደጉን ካልቻሉ ደግሞ ዋናው መፍትሄ የሚጠበቀው ከዋናው የሀገሩ ባለቤት ከኢትዮዽያ ህዝብ መሆኑ የግድ ይሆናል። እየተላለቁ የመፈራረስ አደጋ አፍጥጦ ሲመጣ ተጐጅ የሚሆነው ሁሉም ህዝብ ወይም እያንዳንዱ ዜጋ ስለሆነ ህዝቡ ከመንግስት ወይም ከተቃዋሚዎች መፍትሄ ይመጣል ብሎ በዝምታ መጠበቅ የለበትም። ከእነሱ የሚጠበቀው መፍትሄ እስከ ወዲያኛውም ላይመጣ ስለሚችል እጁን አጣጥፎ በመጠበቅ ራሱን ለህልውና አደጋ ማጋለጥ የለበትም። አንድ ህዝብ ጥቅሙን የሚያውቅና የበቃ የለውጥ ኃይል ነው ሊባል የሚችለው እንዲህ ዓይነት ህልውናን የሚፈታተን አደጋ ሲገጥመው ራሱን ለማዳን በሚዎስደው ወሳኝ የለውጥ እርምጃ ነው። ህዝቡ ከሌሎች የሚመጣን መፍትሄ በከንቱ ከመጠበቅ ይልቅ በራሱ ተነሳሽነት የተለያዩ ህዝባዊ አደረጃጀቶቹን በመጠቀም፣ እርስ-በርሱ በመነጋገርና በየአካባቢው በመሰባሰብ፣ የራሱን አካባቢያዊ መሪዎች በመምረጥ ወይም በመከተል የራሱን ጠንካራና በህዝባዊ እምቢተኛነት የታገዘ አገዛዝ-አንቀጥቅጥ ትግል በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ማካሄድ አለበት። ቢያንስ የሀገሪቱ ሙህራን፣ ወጣቶችና የከተማ ኑዋሪዎች የታጣቂዎችን ነፃ አውጭነት ቁጭ ብሎ ከመጠበቅ “ጦርነት ይብቃ! ሰላም ይምጣ!” በሚለው ወቅታዊ አጀንዳ ዙሪያ በመሰባሰብ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ጠንካራ ትግል ሊያካሂዱ ይገባል።
የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደካማ መሆንም ሆነ የፒያሳና የካዛንችስ ሰፈሮች መፍረስ ህዝባዊ ትግል ላለማድረግ ምክኒያት ሊሆን አይችልም። ለመረጃ ቴክኖለጅ ምስጋና ይግባውና፣ 20 ሚሊየን የኢትዮዽያ የከተማ ኑዋሪዎችን እንደ አንድ ሰፈር የዕድር አባላት በአንድ ጥሩንባ መጥራትና ማንቀሳቀስ የሚቻልበት ዕድል ተፈጥሯል። በአንድ ሀገር መሰረታዊ ለውጥ እንዲመጣ መንግስት፣ ተቃዋሚ ኃይሎችና ህዝቡ በቅደም-ተከተል ወሳኝ ድርሻ አላቸው። አንድ ሀገር ከህልውና ጥፋት ሊድን የሚችለው ከእነዚህ ሶስት ተዋናኞች ውስጥ ሲቻል ሶስቱ፣ ካልተቻለ ሁለቱ፣ ያም ካልተቻለ ቢያንስ አንዱ ኃላፊነቱን ለመወጣት ብቁ ሆኖ ሲገኝ ነው። “አለመታደል” ሆነና በወቅቱ የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሶስቱም አካላት አደጋን የማስቀረትም ሆነ ለውጥን የማምጣት ብቃት ላይ አይደሉም። መንግስትና ተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆኑ ህዝቡ ከማንምና ከመቸውም ጊዜ በላይ ለራሱ ህልውና መታገል የተሳነው ፈሪና ድንዙዝ መናጆ ሆኗል። መንግስትና ተቃዋሚዎች በዚህ መጠን ደካማና ኃላፊነት የማይሰማቸው የሆኑትም በሌላ ምክኒያት ሳይሆን የህዝቡ ድክመት ነፀብራቅ በመሆናቸው ነው። “ህዝብ የሚገባውን ስርዓት ያገኛል” የሚባለውም በዚሁ ተገቢ ምክኒያት ነው። እንደዚህ “ከሶስት አንድ ያጣ” ሀገርና ህዝብ በመሆናችን ምክኒያት ነው- ከመዳን ይልቅ እየተላለቁ የመፈራረስ ዕድላችን የበለጠ አይቀሬ እየሆነ የመጣው።
“ህዝቡ ከሌሎች የሚመጣን መፍትሄ በከንቱ ከመጠበቅ ይልቅ በራሱ ተነሳሽነት የተለያዩ ህዝባዊ አደረጃጀቶቹን በመጠቀም፣ እርስ-በርሱ በመነጋገርና በየአካባቢው በመሰባሰብ፣ የራሱን አካባቢያዊ መሪዎች በመምረጥ ወይም በመከተል የራሱን ጠንካራና በህዝባዊ እምቢተኛነት የታገዘ አገዛዝ-አንቀጥቅጥ ትግል በሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ማካሄድ አለበት። ቢያንስ የሀገሪቱ ሙህራን፣ ወጣቶችና የከተማ ኑዋሪዎች የታጣቂዎችን ነፃ አውጭነት ቁጭ ብሎ ከመጠበቅ “ጦርነት ይብቃ! ሰላም ይምጣ!” በሚለው ወቅታዊ አጀንዳ ዙሪያ በመሰባሰብ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ጠንካራ ትግል ሊያካሂዱ ይገባል። “
2.4. በውጭ ሀገራት ከሚኖረው ኢትዮዽያዊ
በአሁኑ የኢንፎርሜሽን ዘመን በውጭ ሀገራት ኗሪ የሆነው ኢትዮዽያዊ ለሀገር ውስጡ ትግል መጠናከር ከፍተኛ ሚና የመጫዎች ዕድል አለው። በፋይናንስ እርዳታ፣ በመረጃ ፍሰትና ዲፕሎማሲያዊ ጫና በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫዎት ይችላል። ይሁንና “ዳያስፖራው” በእነዚህ የበለጠ ውጤታማ ሊሆንባቸው የሚችሉ እገዛዎች ዙሪያ ትርጉም ያለውና ጠንካራ ስራ ከመስራት ይልቅ የሀገር ውስጡን ትግል በበላይነት መምራት እያማረው፣ የሚኖረውን የትግል ሚና በብዙ እጅ አሉታዊና ትግሉን የበለጠ የሚያዳክም አድርጐታል። ዳያስፖራው- የሀገር ውስጡን ትግል ወደ መሰባሰብ ከመግፋት ይልቅ በአክራሪ የብሄርተኛነትና የአውራጃዊነት ስሜት የበለጠ በመከፋፈል፣ ሰላማዊ ትግሉን ከማበረታታት ይልቅ የፅንፈኝነትና የጦረኝነት ፖለቲካን የበለጠ በማጠናከር፣ የዘመኑ ማህበራዊ ሚዲያ የፈጠረውን እድል በአግባቡ በመጠቀም የሰለጠነ የሀሳብ ፖለቲካን ከማራመድ ይልቅ አሉባልታና የጥላቻ ንግግርን በማስፋፋት፣ በእነዚህና እነዚህን በመሰሉ ሌሎች አሉታዊ ድርጊቶቹ የወቅቱ ትግሉ በዲፕሎማሲው ዓለም የሚደገፍና የሚከበር ሳይሆን የተናቀና በስጋት የሚታይ እንዲሆን አድርጐታል።
ይህንን ዕውነታ በመገንዘብ ዳያስፖራው በሀገር ውስጡ ትግል ከአግባብ በላይ ጣልቃ እየገባ ከፋፋይና ችግር ፈጣሪ ከመሆን ይልቅ በሰላምና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ዙሪያ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ቢሰራ በአገዛዙ ላይ ትርጉም ያለው ጫና ሊፈጥር ይችላል። በተለይም በአሁኑ ወቅት የጦርነት ደጋፊ ሆኖ ከመቆም ይልቅ “ጦርነት ይብቃ! ሰላም ይምጣ!” የሚለው ወቅታዊ አጀንዳ ዋና ባለቤት በመሆን ጠንካራና ትርጉም ያለው የዲፕሎማሲ ትግል ቢያደርግ በአገዛዙ ላይ ጠንካራ ጫና በመፍጠርና እየተላለቁ የመፈራረሱን አደጋ በማስቀረት ረገድ ትልቅ ሚና ሊጫዎት ይችላል። በአሁኑ ዘመን የጦረኝነትና የብሄርተኛነት አጀንዳ ተሸካሚ ሆኖ ከምዕራቡ ዓለም አክብሮትና ድጋፍን ማግኘት የሚቻል አይደለም። ይህንን መገንዘብ ተስኖት ዳያስፖራው አሁን በያዘው መንገድ መቀጠልን የሚመርጥ ከሆነ ግን በትግሉ ውስጥ ከመኖሩ ይልቅ አለመኖሩ ይመረጣል ባይ ነኝ። ከዚህ በላይ ለማየት እንደተሞከረው በትግሉ ውስጥ ዓይነተኛ ተዋናይ የሆኑት ሁሉም ኃይሎች ከጥንካሬአቸው በላይ ድክመታቸው የበዛ፣ የለውጥ ኃይል ከመባል ይልቅ የለውጥ እንቅፋት መባል የበለጠ የሚገልፃቸው ናቸው። ሀገራዊ ትስስርን የሚበጣጥስና ህዝብን ዕርስ-በርስ የሚያጫርስ ተግባር እየፈፀምን እየዋልን- በተቃራኒው “ኢትዮዽያችን አትፈርስም” እያልን ለመከራከር መሞከር አጉል ግብዝነት ይሆናል። እኛ አፍራሽ ስራ እየሰራን በተቃራኒው ሀገሪቱ ሳትፈርስ ከቀረችም ይህ ሊሆን የሚችለው በኛ ብርታትና ጥረት ሳይሆን፣ ተገቢ ፍች ልንሰጥበት በማንችል የራሷ “እንቆቅልሽ” ይሆናል።
2.5. ከኤርትራ መንግስትና ህዝብ
ኢትዮዽያ እና ኤርትራ በብዙ መስተጋብርና በታሪክ አንድ ከነበረ ህዝብ የተፈጠሩ ሁለት ሀገራት ስለሆኑ ተለያይተውም መለያየት አልቻሉም። ይህ እውነታ በመካከላችን ዘላቂ የሰላምና የትብብር ግንኙነት እንዲኖረን የሚያስገድድ ቢሆንም ሁላችንም “ከአንድ ድፍርስ ወንዝ የተቀዳን” ነንና በጠብና በግጭት ውስጥ መኖርን መርጠናል። የእስካሁኑ መዋጋታችን ያስከተለው እልቂትና ውድመት አልበቃን ብሎ፣ ዛሬም ለሌላ ዙር የበለጠ አውዳሚ የሚሆን ጦርነት እየተዘጋጀን እንገኛለን። ከመከራ መማር የምንችል አይደለንምና ተጠፋፍተን ካላለቅን በስተቀር መቸም ቢሆን እርስ-በርስ መዋጋት የሚበቃን አይመስልም። ከወቅቱ የጦርነት ውጥረት ጋር በተያያዘ የኤርትራ መንግስት እንደ ልማዱ በኢትዮዽያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ልበጥብጥ ካላለ በስተቀር ራሱን ከጥቃት የመከላከል መብት ያለው መሆኑ ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ነገር ግን ገና ጥቃት ሊሰነዘርብኝ ይችላል ከሚል ስጋት፣ ወይም እንደለመደው ሀገሪቱን ለማዳከም የሚያስችለኝ የተሻለ እድል ዛሬ ነው በሚል የተሳሳተ እሳቤ ኢትዮዽያን ቀድሞ ወደ መውጋት አጉል መቀናጣት በፍፁም መግባት የለበትም። ከእንግዲህ ሊነሳ የሚችለው ጦርነት በኢትዮዽያ ብቻ ተወስኖ የማይቆም፣ የራሷን የኤርትራን ህልውናም ጭምር አደጋ ላይ የሚጥል ሊሆን ስለሚችል ስለሚያስከትለው ጣጣ ሁለት-ሶስት ጊዜ ቆም ብሎ ማሰብን ይጠይቃል። ስለዚህ የኤርትራ መንግስት ለማንም ብሎ ሳይሆን ለራሱ ህልውና መቀጠል ሲል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የተንኳሽነት ሚና ውስጥ ባለመግባት ሊፈነዳ የተቃረበውን አደገኛ ጦርነት ለማስቀረት የራሱን ሚና ሊጫዎት ይገባል። ከሁሉም በላይ መከረኛው የኤርትራ ህዝብ “ጦርነት ይብቃ፣ ሰላም ይምጣ!” የሚለውን ወቅታዊና አንገብጋቢ አጀንዳ በአደባባይ ደግፎ ለመቆም ለመጀመሪያ ጊዜ ሊደፍር ይገባል። ይህ የመሆን ዕድሉ እጅግ ጠባብ እንደሆነ ይገባኛል። ግን…የኤርትራ ህዝብ በአደባባይ “ጦርነት በቃን!” ብሎ መታገል የሚጀምረው በኤርትራ ምድር ስንት ሰው በህይዎት ሲቀር ነው? የኤርትራ ህዝብ በሁለንተናዊ መመዘኛ ሀገር-የለሽ ባደረገው አንድ አምባገነን መሪ እየተገዛ እስከ መቸስ ነው በሉዓላዊነት ሰበብ ልጆቹን በጦርነት እያስጨረሰ የሚቀጥለው? በእኔ ዕይታ፣ ኤርትራዊያን ትርጉም አልባ ከሆነ “የሉዓላዊነት ማስከበር” እግረ-ሙቅ ተላቃችሁ የአቶ ኢሳያስ አፈወርቄን የዕድሜ ዘመን የሚሻገር ሀገርና ህልውና እንዲኖራችሁ በሚያስችል አግባብ ማሰብና መታገል ያለባችሁ ይመስለኛል። በተለይም በውጭ ሀገራት የምትኖሩ ኤርትራውያን ከእርስ-በርስ ብሽሽቅና ፉክክር ወጥታችሁ ለህዝባችሁ የሚመጥን የበሰለ ትግል በሀላፊነት ስሜት ልታካሂዱ ይገባል። ራሳችሁንና ልጆቻችሁን በተሻለ ኑሮ እያኖራችሁ የአቶ ኢሳያስ የፍፁማዊ አገዛዝና የጦርነት ደጋፊ ሆኖችሁ መኖር ከሞራልም ሆነ ከፖለቲካዊ አመክኒዮ አኳያ ስህተት ብቻ ሳይሆን ትልቅ ነውርም ነው። የእናንተ ልጆች የውጭ ሀገር ህይዎትና ኑሮ ለኤርትራ ህፃናትና ወጣቶችም እንደሚያስፈልጋቸው አትዘንጉት። በውጭ ሀገር ሆናችሁ አቶ ኢሳያስንና ጦርነትን ስትደግፉ፣ እናንተ ጥላችሁት በመጣችሁት በኤርትራ ውስጥ በሚኖሩ ህፃናትና ወጣቶች ህይወት ላይ እየፈረዳች መሆኑን ተገንዘቡ።
2.6. ከምዕራባዊያን
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምዕራባዊያኑ ለብልፅግና መንግስት ያላቸው አመለካከት በተወሰነ ደረጃ መቀየር ጀምሯል። ከራሳቸው ጥቅም አኳያ ከምንም ነገር በላይ የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት የሚያስጨንቃቸው ምዕራባዊያን በጐ ስርዓት ነው ብለው በማመን ሳይሆን በተቃዋሚዎቹ ድክመትና መከፋፈል ተስፋ በመቁረጥ ብቻ የብልፅግናን አገዛዝ ደጋግፎ በስልጣን ላይ ማክረም የተሻለ አማራጭ አድርገው ማሰብ የጀመሩ ይመስላል። ከዚህ የተዛባ አስተሳሰብ በመነሳት- አገዛዙ በተቃዋሚዎቹ የትግል ብርታት ሳይሆን ቢያንስ በኢኮኖሚ ቀውስ ምክኒያት የመፈረካከስ አደጋ እንዳይገጥመው በመስጋት እርዳታና ብድር እየሰጡ ሊያከርሙት ሲሞክሩ እየታዬ ነው። በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ሊፈነዳ ስለተቃረበው አደገኛ ጦርነትም ተገቢ ትኩረት ሰጥተው የማስቀረት ጥረት ሲያደርጉ እየታየ አይደለም።
ምዕራባዊያን ከራሳቸው ስትራቴጅክ ጥቅም አኳያ ለጊዜው እየወሰዱት ያለው አቋም ስህተት ነው ባይባልም፣ ከዘላቂ መፍትሄ አንፃር ግን የወቅቱን አገዛዝ በማገዝና በስልጣን ላይ በማቆየት እንዳይመጣ ብለው የሚሰጉትን አደጋ በዘላቂነት ሊያስቀሩት አይችሉም። ይኸ አገዛዝ የከፋፋይነት፣ የአፈናና የጦረኝነት ፖሊሲውን ይዞ በስልጣን ላይ ውሎ እስካደረ ድረስ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ምዕራባዊያኑ ይከሰታል ብለው የሚሰጉት የኢትዮዽያ መፍረስም ሆነ የምስራቅ አፍሪካ መተራመስ አይቀሬ ነው። ተቀናቃኞቹ ደካማ መሆናቸውን በማዬት ብቻ በብዙ ወንጀል የተዘፈቀና ጦርነትን ቋሚ የአገዛዝ ስልቱ ያደረገን የብልፅግና አገዛዝ ደግፎ በስልጣን ለማቆየት መሞከር ከሞራል፣ ከፍትህ፣ ከዲፕሎማሲም ሆነ የራስን ጥቅም በዘላቂነት ከማስጠበቅ አኳያ እጅግ የተሳሳተ አቋም ነው። ይልቁንም የተሻለ የሚሆነው- አገዛዙ በእውነተኛ ድርድር ከተፋላሚዎቹ ጋር የተኩስ ማቆም ስምምነት ተፈራርሞ ሰላም እንዲያሰፍን፣ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንዲመጣም በሀገሪቱ እውነተኛ መግባባትና ሁሉን-አቀፍ የሆነ አዲስ የሽግግር ሂደት እንዲፈጠር በአገዛዙና በተቃዋሚዎች ላይ አስፈላጊውን ጫናና ግፊት መፍጠር ነው። ከዚህ ውጭ የወቅቱን አገዛዝ በስልጣን ላይ በማስቀጠል በሀገሪቱም ሆነ በአካባቢው ሊመጣ የሚችለውን እየተላለቁ የመፈራረስ አደጋ አይቀሬ ማድረግ እንጂ ማስቀረት አይቻልም። ምዕራባዊያኑ በአካባቢያችን ስላለው ነባራዊ ሁኔታ የቀረበ ግምገማ ያላቸው አይመስልም። በአሁኑ ወቅት በአካባቢው እየመጣ ያለው አዲስ የኃይል አሰላለፍ ለውጥ እያሳየን ያለውም ከነሱ ግምት ውጭ እየተላለቁ የመፈራረሱ አደጋ የበለጠ አፍጥጦ እየመጣ መሆኑን ነው። ይህ አደጋ እንዳይመለስ ሆኖ ከመፈንዳቱ በፊት ምዕራባዊያን ለችግሩ በሚመጥን መጠንና ፍጥነት ጦርነቱን ለማስቆም መረባረብ አለባቸው። አሁን ላይ በሱዳን፣ በሱማሊያና በደቡብ ሱዳን ባለው ችግር ላይ የኢትዮ-ኤርትራ ሌላ ጦርነት ከፈነዳ አካባቢው ከቁጥጥር ውጭ መውጣቱ የማይቀር ነው። ዳያስፖራው በዲፕሎማሲው ትግል የወደቀውን ፈተና በውል ተገንዝቦ በፍጥነት የተሻለ ግፊት መፍጠር ካልቻለ በዲፕሎማሲው ረገድም እየተገዳደሉ የመፈራረሱን አደጋ ለማስቀረት የሚረዳ ድጋፍ ማግኘት የሚቻል አይሆንም።
ክፍል 2 ይቀጥላል
ኦሮማይ!! ጦርነት ይብቃ!፣ ሰላም ይምጣ!
ልደቱ አያሌው
ሚያዚያ 28 ቀን 2017 ዓ.ም




