"የዲጂታል ሥርዓቱን በማኑዋል የመተካት ህገወጥ ስራ እና የጉልበት ብዝበዛ በምርጫ ሂደቱ እየተስተዋለ ነው" ተስፋ ተ. ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- በአሁኑ ወቅት በምርጫ ቦርድ ስም እየተከናወነ ያለው የመራጮች ምዝገባ ሂደት ከዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይልቅ ወደ ግዴታና ወደ ጉልበት ብዝበዛ የተቀየረ ይመስላል።
እኔ እንደ አንድ ነፃ ታዛቢ እና የዜጎች መብት ያሳስበኛል እንደምል ግለሰብ የሚከተሉትን ህገ-ወጥ ድርጊቶች አጥብቄ እቃወማለሁ፡
1. የዲጂታል ሥርዓቱን በ"ማኑዋል" የመተካት ስራ የምርጫ ቦርድ የዲጂታል ምዝገባ ሥርዓት የዘረጋው ሂደቱ ግልጽና ተዓማኒ እንዲሆን ነበር። ይሁን እንጂ አሁን እየታየ ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ነው። ኔትወርክ ጠፍቶ ሳይሆን ዲጂታሉ ሥርዓት በሕጉ የተቀመጡትን መስፈርቶች በሙሉ ስለሚጠይቅ እና የተጭበረበረ ምዝገባን ስለማይፈቅድ ይህንን የሕግ አጥር ለማለፍ ሲባል ወደ "ማኑዋል" (በወረቀት) ምዝገባ ተመልሷል። ይህ አሰራር የምርጫውን ተዓማኒነት ዜሮ የሚያደርግና ለታለመለት የጭበርባሪ አሰራር በር የሚከፍት ነው።
2. የቀበሌ ሠራተኞች ጣልቃ ገብነትና የዜጎች መብት ረገጣ: ምዝገባው በምርጫ ጣቢያዎች በነፃ ፈቃድ መከናወን ሲገባው በአሁኑ ወቅት የቀበሌ ሠራተኞች ዜጎችን ከሥራ ቦታቸውና ከቤታቸው እያስገደዱ እንዲመዘገቡና ካርድ እንዲወስዱ እያደረጉ ይገኛሉ። ይህ የዜግነት መብት ጥሰት ነው፣ መመዝገብ መብት እንጂ ግዴታ አይደለም። አንድን ዜጋ ከሥራ ገበታው አፈናቅሎ "ካርድ ውሰድ" ብሎ ማስገደድ ሕገ-መንግሥታዊ መብትን በግልጽ መጣስ ነው።
3. የቦርዱ ገለልተኝነት፦ የምርጫ ቦርድ ነፃ ተቋም ሆኖ ሳለ የቀበሌ (የአስፈፃሚው አካል) ሠራተኞች ሂደቱን እንዲመሩት መደረጉ የምርጫውን ገለልተኝነት ሙሉ በሙሉ ያጠፋዋል።
4. በሥራ አስፈፃሚዎች ላይ እየደረሰ ያለ የጉልበት ብዝበዛ ቦርዱ ያለምንም ተጨማሪ ክፍያ የምዝገባ ቀናትን አራዝሟል። እነዚህ ሠራተኞች ውላቸው 54 ቀን ሆኖ ሳለ አሁን ወደ 68 ቀናት እንዲሠሩ መገደዳቸውና ላለፉት 38 ቀናት (አንድ ወር በምዝገባ ላይ እና 8 ቀን በስልጠና ላይ) እንኳን የሠሩበት አበል አለመከፈሉ ግልጽ የጉልበት ብዝበዛ ነው። በኢትዮጵያ የሥራ ሕግ እና በዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) ስምምነቶች መሰረት ያለ ክፍያና ያለ ሠራተኛው ፈቃድ የሥራ ጊዜን ማራዘም "አስገዳጅ ሥራ" (Forced Labor) ተብሎ የሚፈረጅ ወንጀል ነው።
ለማጠቃለል፣ የምርጫ ካርድ መውሰድ የዜጎች የነፃ ፈቃድ ውጤት መሆን አለበት። ዲጂታሉ ሥርዓት "አልመዘግብም" ያለውን መረጃ በማኑዋል ለመመዝገብ መሞከር የሕግ ጥሰት ነው። እንዲሁም የሠራተኛውን ላብ ሳይከፍሉ ለሳምንታት ማሰራት በየትኛውም የሞራልም ሆነ የሕግ መለኪያ ተቀባይነት የለውም።
የሚመለከታቸው አካላት ይህንን ሕገ-ወጥ አሰራር በአስቸኳይ እንዲያቆሙና የሠራተኛውንም ሆነ የዜጎችን መብት እንዲያከብሩ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
-መሠረት ሚድያ-


