የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን እንደ ሽፋን: የፍርድ ቤቶች የውድቀት መሳሪያ ስናይፐር
(መሠረት ሚድያ)- አገልግሎት የማይዳሰስ እና የማይጨበጥ የሆነ እና ተገልጋይ ለተባለ ሰው የሚሰጥ ነው፡፡ ይህ አገልግሎት በተለያዩ ተቋማት የተለያዬ እይታ ያለው እና እንደ ነባራዊ ሁኔታው እና ተቋሙ እንደተቋቋመበት ዓላማ የሚወሰን ነው፡፡
አገልግሎት በመከላከያ ተቋም፣ በደህንነት ተቋም፣ በፖሊስና በፀጥታ ተቋም የሚኖረው ባህሪ እና አገለግሎት በባንኮች፣ በመድን ሰጭ ተቋማት እንዲሁም በሆቴሎች የሚኖረው ባህሪ በእጅጉ ይለያል፡፡
በእነዚህ በተጠቀሱት የመንግስት ተቋማት ውስጥ አገልግሎት በባህሪው ጥብቅ እና ተቋሙን ባስከበረ መልኩ የሚከወን ሲሆን ከላይ በተጠቀሱት እና ለትርፍ በተቋቋሙ ተቋማት ላይ ደግሞ ደንበኛ ንጉስ የሚሆንበት፣ ደንበኛ አይሳሳትም የሚል መርህ የሚተገበርበት ቅድሚያ ለተገልጋዩ የሚሰጥበት ሁኔታ ይታያል፡፡
ስለዚህ የአገልግሎት አሰጣጥ እንደ ተቋሙ ባህሪ የሚለያይ በመሆኑ በሁሉም ተቋም ተመሳሳይና ወጥአገልግሎት መሰጠት የማይቻል መሆኑ የአለም ሁኔታ የሚያረጋግጠው ነባራዊ ሀቅ ነው፡፡
በፍርድ ቤት በኩል የሚሰጡ አገልግሎቶችምራሳቸውን የቻሉ ባህሪዎች ያሏቸው መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች የተቋቋሙበት ዋና ዓለማ በህግ መሰረት አለመግባባቶችን ለመፍታት እና ፍትህ ለማስፈንነው፡፡ ዜጎች ህገ መንግስታዊ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው እና ተጥሰው ሲገኙም መብቶቻቸውን ለማስከበር እንዲችሉ ፍርድ ቤቶች ሊቋቋሙ ችለዋል፡፡
ፍርድ ቤቶች ዘንድ የሚመጡት ተገልጋዮች አንድም በወንጀል ተጠርጥረው ወይም ተከሰው በሌላ በኩልደግሞ በፍታብሔር ክስ ጉዳይ ተከራካሪ ሆነው እንዲሁም በወንጀል ድርጊት የተጎዱ ሰወች እና ምስክሮች፣ ችሎት ለመታደም በሚል ምክንያት የሚመጡ ሰዎች ናቸው፡፡
የፍርድ ቤቱም ዋና ራዕይ በሚሰጠው አገልግሎት የተበደሉ ፍትህ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ያጠፉ ሰዎች የሚቀጡበት እና ሌሎች ሰዎች ደግሞ በፍርድ ቤቱ አሰራር እና ውሳኔ ትምህርት እንዲወስዱ ማድረግ ነው፡፡ ፍርድ ቤቶች እንደ ሆቴሎች፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ሌሎች ለትርፍ እንደተቋቋሙ ተቋማት ተገልጋዮችን በመንከባከብ እርካታ እንዲያገኙ የማድረግ ዓላማም ግዴታም የለበትም፡፡ የፍርድ ቤት ተገልጋይ ንጉስ ነው፣ ንጉስ ደግሞ አይሳሳትም በሚል ብሂል የሚስተናገድ ሳይሆን ግዴታውን በህግ መሰረት እየተወጣ መብቱን ሰብዓዊ ክብሩ ተጠብቆለት እንዲጠቀም ማስቻል ነው፡፡
የፍርድ ቤት ተገልጋይ ሊሳሳት የሚችል እንጂ ፍፁም የማይሳሳት ተደርጎ የማይወሰድ ሲሆን ተሳስቶ ሲገኝ በህግ መሰረት ቅጣት የሚጣልበት እንጂ እንደ ሆቴል ተገልጋይ እሹሩሩ የሚባልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ አንድ የፍርድ ቤት ተገልጋይ የፍርድ ቤቱን ህግና ስርዓት አክብሮ የመንቀሳቀስ ግዴታ አለበት፡፡ ይህን ግዴታ አለመወጣት ደግሞ ህጋዊ ውጤት የሚያመጣበት ይሆናል፡፡
ይሁን እንጂ አሁን አሁን በተገልጋዩ ማህበረሰብ ዘንድ ፍርድ ቤትን ለትርፍ እንደተቋቋመ ድርጅት ተገልጋዩን እያቀበጠ ጠብ እርግፍ እያለ አገልግሎት መስጠት ግዴታ ያለበት ተደርጎ የመወሰድ ሁኔታ የተፈጠረ እና በፍርድ ቤቱ ሰራተኞች እና ዳኞች ላይ ተገቢ ያልሆነ ጫና ለማሳደር ጥረት በመደረግ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ አዝማሚያ በአንዳንድ አመራሮች ዘንድም በጉልህ የሚደገፍ እና የሚቀነቀን ሚዛን የሳተ አሰተሳሰብ በመሆን ላይ ይገኛል፡፡
የፍርድ ቤት ተገልጋይ ፍርድ ቤት ሲመጣ የማንንም ሰው መብት የማክበር ግዴታ ያለበት መሆኑን መረዳት እና መማር የሚገባው ሆኖ እያለ እንዲሁም ህግና ስርዓትን ማወቅ እና መማር የሚችልበት ሁኔታ ሆኖ እያለ በተቃራኒው የፍርድ ቤቱን ማህበረሰብ ለመቆጣጠር እና ስርዓት ለማስያዝ በሚመስል መልኩ ስም ማጥፋቶች፣ ማንጓጠጦች፣ ሁከትና ብጥብጥ መፍጠር፣ በየኃላፊዎች ክስና አቤቱታ በማቅረብ ማስጨነቅ፣ ፍርድ ቤቱ ህጋዊ አገልግሎት ለመስጠት የዘረጋቸውን አሰራሮች እና አደረጃጀቶች በመጠቀም ጫና ለማድረግ መጣር እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ አሉታዊ ጫናዎችን በመፍጠር የሚፈልጉትን ጉዳይ ለማስፈፀም ጥረት የማድረግ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ፡፡
አሁን አሁን ፍርድ ቤቶች ህግና ስርዓት የሚከበርባቸው መሆኑ ቀርቶ ተገልጋዮች ፍርድ ቤቶችን እንደ መጠቀሚያ በማድረግ ህግና ስርዓት አልበኝነት እንዲሰፍን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ የፍርድ ቤቱን ማህበረሰብ በአገልግሎት አሰጣጥ ስም በማስፈራራት እና በሙስና እንዲዘፈቅ የማታለያ እና የማባበያ ዘዴዎችን በማቅረብና በመስጠት ንፁሀን ዳኞችና ሰራተኞች እንዲሸማቀቁ በማድረግ ፍርድ ቤቶቹን ሽባ የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
የአስተዳደር ሰራተኞችን ከቅርብ ኃላፊ እስከ ከፍተኛ የፍርድ ቤቱ አመራሮች ዘንድ በመክሰስና በማዋካብ ሰራተኞች ደግሞ ከክስና ከእንግልት ለመገላገል በሚል ተገልጋዩ የሚፈልገውን ህገወጥ ድርጊት በመፈፀም ተባባሪ የመሆን ሁኔታ በሰፊው ተንሰራፍቷል፡፡ ቅሬታ የሚቀርብለት ኃላፊም ጉዳዩን በአግባቡ ሳይመረምር ቅሬታ አቅራቢ ፊት ሰራተኛን በመገሰፅ እና የጥፋተኝነት ውሳኔ በመወሰን ተገልጋዩን አክብሮ መያዝ እንዳለበት ውሳኔ የመስጠት ልማድ ያለበት በመሆኑ ሰራተኞች የተቋሙን እሴት ለማስጠበቅ ፍቃደኝነት እንዳይኖራቸው ተደርጓል፡፡
ዳኞችንም በተመለከተ አንድ ተገልጋይ ከህግና ስርዓት ውጭ ሲንቀሳቀስ ዳኞች ስርዓት ለማስያዝ የሚያደርጉትን ምክር፣ ተግሳፅ እና የችሎት መድፈር ሁኔታ ሲያጋጥም የሚሰጡትን ቅጣት በተመለከተ ዳኛው ተገልጋዩ ላይ ተፅዕኖ እንዳደረገ በማድረግ የስም ማጥፋት ዘመቻ የሚደረግበት እና ከዝቅተኛ የአመራር እርከን ጀምሮ እስከ ፍርድ ቤቱ የበላይ አመራሮች እና የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ ድረስ ክስ በማቅረብ የማሸማቀቅና ዝም የማሰኝት ድርጊቶችን በመፈፀም ላይ ይገኛል፡፡
የፍርድ ቤቶች የበላይ አመራሮችም ሆነ ጉባኤው በፍርድ ቤቶች ላይ ያለውን ዘመቻ እና በማስፈራራት የሚፈልጉትን የማስወሰን አካሄድ ባለማጤን በዳኞች ላይ ክሶችን በመቀበል የማዋከብና የማስፈራራት ሁኔታ ያለ በመሆኑ ዳኞች ከዚህ ሁሉ ጣጣ ለማምለጥ ከባለጉዳዮች ጋር ቸበርቻቻ እያሉ መዋል ማደርን መርጠዋል፡፡
ይህ ደግሞ ፍርድ ቤቶች በሙስናና በብልሹ አሰራር እንዲዘፈቁ በር ከፍቷል፡፡ በመሆኑም የፍርድ ቤት አገልግሎት ህግና ስርዓትን መሰረት በማድረግ የሚሰጥ እንደመሆኑ መጠን ተገልጋዮች ለህግና ስርዓት እንዲገዙ የማድረግ ስራ በተለይም የፍርድ ቤቱን ሰራተኞች እና ዳኞችን የማክበር ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥብቅ አሰራር ሊዘረጋ ይገባል፡፡ ፍትህ ህግና ማስረጃን ከእውነት ጋር በማጣመር ይሰፍን ዘንድ የፍርድ ቤቱን አገልግሎት አሰጣጥ በማዘመን ጎን ለጎን ተገልጋዩን ህብረተሰብ ህግና ስርዓት ማስያዝ ጊዜ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ አይደለም፡፡
ይህ ጉዳይ በትኩረት ካልተሰራበት ፍርድ ቤቶች ህገ መንግስቱ የሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት እና ለህብረተሰቡ ፍትህ መሰጠቱ ቀርቶ ሙሉ በሙሉ የአጭበርባሪ ዜጎች መፈንጫ የሚሆንበት ጊዜ ሩቅ የማይሆበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በአጠቃላይ ሀቀኛ የፍርድ ቤቱ ተገልጋዮች፣ መንግስት እና ህዝብ ፍርድ ቤቶች ነፃና ገለልተኛ ሆነው ስራቸውን እንዲሰሩ ፍርድ ቤቱን ከውስጥና ከውጭ አጭበርባሪዎች መጠበቅ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃላፊነት ያለባቸው ጊዜ ላይ መሆናቸውን ጠንቅቀው በመረዳት ወደ ተግባር መግባት ይገባቸዋል፡፡
ቸር እንሰንብት
(ስሜ አይጠቀስ ባሉ አስተያየት ሰጪ ለመሠረት ሚድያ የተላከ)



