ከበርካታ ግለሰቦች ብዙ ሚሊየን ብር ተቀብሎ የተሰወረው ኢትዮጵያዊ ናይሮቢ ውስጥ እየተፈለገ ነው
(መሠረት ሚድያ)- በዚህ የኢንተርኔት ዘመን በርካቶች የተለያዩ የማጭበርበርያ ዘዴዎችን በመጠቀም ህብረተሰቡን ሲዘርፉ ይስተዋላሉ፣ ድርጊቱ በተለይ ማህበራዊ ሚድያ ላይ በስፋት ሲፈፀም ይስተዋላል።
አንዳንዶች በፒራሚድ አሰራር እቃዎችን ግዙ ተብለው ከገቡ በኋላ ገንዘባቸው ይወሰድባቸዋል፣ ሌሎቹ ደግሞ 'ውጭ ሀገር የተቀመጠ ገንዘብ ስላለን ለማውጣት ተባባረን' በሚል ጥያቄ መነሻነት ይዘረፋሉ።
ዛሬ የምናስነብባችሁ ግን ከዚህ ለየት ያለ እና ትንሽ ረቀቅ ባለ መልኩ በአንድ ኢትዮጵያዊ የሀገሩ ዜጎች እና የውጭ ሀገር ግለሰቦች ላይ ኬንያ ሀገር ውስጥ በቅርቡ የተፈፀመ የማጭበርበር ድርጊትን ነው።
ግለሰቡ ዳንኤል ሙሉነህ ይባላል። የ26 አመቱ ዳንኤል ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ሲሆን ኑሮውን በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ካደረገ ሰነባብቷል።
ታድያ ግለሰቡ በቅርብ ወራት የፈፀመው አንድ ድርጊት የብዙዎች መነጋገርያ አድርጎታል።
ግለሰቡ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች ጋር አብሮ እንደሚሰራ በመግለፅ ሰዎችን ቀድሞ ያሳምናል። ከዛም ሰዎችን ወደ ካናዳ ሀገር እንደሚልክ በመግለፅ ከበርካታ ግለሰቦች ከ1.5 ሚልየን ብር እስከ 2.4 ሚልየን ብር እንደተቀበለ ሚድያችን ያሰባሰበው መረጃ ያሳያል።
ዳንኤል ድርጊቱን ሲፈፅም ለማሳመኛነት እውነተኛ የሚመስሉ እና እሱ የላካቸውን ሰዎች የሚያሳይ ሰነድ ለተበዳዮቹ ያሳያል፣ ሊሄዱ የተዘጋጁ ሰዎች ናቸው በማለትም አንዳንድ ሰዎችን ናይሮቢ ባለ አንድ አፓርትመንት ያስቀምጣል።
"አሁን ሲገባኝ እነዚህ በአፓርትመንት የተቀመጡ ሰዎች በትክክል ሊሄዱ ሳይሆን እንደ እኛው የወንጀሉ ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ፣ ወይም ሆን ብሎ እኛን ለማሳመን ያደረገው ድርጊት ነው" ያሉን አንድ የድርጊቱ ሰለባ ናቸው።
ኢትዮጵያዊው በዚህ መልኩ የበርካቶችን ገንዘብ ከወሰደ በኋላ ኬንያ ውስጥ ደብዛው እንደጠፋ የታወቀ ሲሆን የኬንያ ፖሊስ መራጃው ደርሶት ፍለጋ እያካሄደ መሆኑ ታውቋል።
ሌላ ግዜ ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ ነኝ ብሎ እንደሚያስነግር፣ ያለበትን ግን እስካሁን ማወቅ እንዳልተቻለ እነዚህ ተጎጂዎች ለሚድያችን ተናግረዋል።
"ለወዳጅ ዘመዶች ህይወት መለወጥ በማሰብ ለዘመናት ሰርተው ያፈሩትን ገንዘብ በርካቶች ተነጥቀዋል፣ ቢያንስ ገንዘቡ ባይገኝ ሌላ ሰው በዚህ ግለሰብ እንዳይጭበረበር መልዕክት አድርሱልን" በማለት ተናግረዋል።
በቅርብ ግዜያት በተለይ ቲክቶክ፣ ዩትዩብ እና ቴሌግራም በመጠቀም ካናዳ ልከን ትምህርት እንዲሁም ስራ እናመቻቻለን የሚሉ ግለሰቦች በርካቶችን ገንዘብ እያጭበረበሩ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይሰማል።
ካናዳ የሰው ሀይል ሲያስፈልጋት በመንግስት ተቋሞቿ እና አብራቸው በምትሰራቸው ኤጀንሲዎች በኩል እንጂ በደላሎች ወይም በቲክቶክ እና ቴሌግራም በሚያስተዋውቁ ግለሰቦች እንዳልሆነ የካናዳ ኤምባሲ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ቼክ ለተባለው የመረጃ ማጣርያ ተቋም አሳውቆ ነበር።
ኤምባሲው በወቅቱ እንዳስረዳው “ህጋዊ በሆነ መልኩ ስራዎቻቸውን ማስተዋወቅ የሚችሉት የተፈቀደላቸው ወኪሎች ብቻ ናቸው” ብሏል።
“ክፍያ ከሚቀበሉ፣ ነገር ግን ካልተፈቀደላቸው ወኪሎች ጋር አንሰራም” የሚለው ደግሞ ስለ ወኪሎች የሚያብራራው የኤምባሲው የድረ-ገጽ ክፍል ነው።
ወኪሎች የተፈቀደላቸው ናቸው የሚባሉት በካናዳ ባሉ ሶስት የህግ ማህበራት ውስጥ መስፈርቶችን አሟልተው አባል የሆኑ እንደሆነ ብቻ እንደሆነም ያብራራል።
የካናዳ ጉዞዎችን በተመለከተ የበለጠ ለመረዳት ከዚህ በታች ያለውን ሊንክ ይከተሉ እና ራስዎን ከአላስፈላጊ ወጪ ይጠብቁ። https://www.canada.ca/en/immigration-refugees-citizenship/services/immigration-citizenship-representative/learn-about-representatives.html
-መሠረት ሚድያ-



