በሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከባለፈው ሁለት ሳምንት ወዲህ ግብፅ ውስጥ በገፍ እየታሰሩ መሆኑ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ከሁለት ወራት በፊት ጀምሮ በግብፅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በኃይል ታፍሰው ወደ ተለያዩ እስር ቤቶች ተወስደው እየታጎሩ መሆኑን በካይሮ የሚኖሩ ስደተኛ ዜጎች ለመሠረት ሚዲያ ተናገሩ።
ለስራ እንደወጡ መንገድ ላይ በግብፅ የፀጥታ አካላት የተወሰዱ እናቶች ከጨቅላ ልጆቻቸው ጋር ጭምር ከተለያዩ ሁለት ወር ያለፋቸው ሲሆን የት እንደተወሰዱም ልናውቅ አልቻልንም ይላሉ።
ገና እድሜያቸው ያልደረሱ ታዳጊዎች ሳይቀር ታፍነው ተወስደዋል የሚሉት ስደተኞቹ ሕጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ኢትዮጵያውያንም ጠፍተዋል ሲሉ ለሚዲያችን ተናግረዋል።
በግብፅ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ቢሮ ስደተኛ መሆናቸውን አረጋግጦ የሰጣቸው መታወቂያ ሳይቀር በፀጥታ ኃይሎች እየተቀደደ ወደ እስር ተወስደዋል ሲሉም አክለዋል።
ቀደም ሲል በዋና ከተማዋ ካይሮ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በንግድ ስራ እና ሰው ቤት ተቀጥረው በመስራት ይተዳደሩ እንደነበር የገለፁት እነዚሁ የመሠረት ሚዲያ ምንጮች በአሁኑ ወቅት ልጆቻቸው ሳይቀር ከትምህርት ገበታቸው ተገልለው በቤት ውስጥ ተዘግተው እንደሚውሉ ነው የተናገሩት።
የኃይል አፈሳ እየተፈፀመ ያለው በኢትዮጵያውያን እና በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ብቻ መሆኑን እና ኤርትራውያን በኤምባሲያቸው አማካኝነት ወደ አገራቸው እየተሸኙ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ግን ገና የታሰሩበት አድራሻ እንኳ ማወቅ አልተቻለም ብለዋል።
ይህንኑ አስመልክቶ በግብፅ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲጠይቅልን በተደጋጋሚ ብናመለክትም ሰሚ አላገኘንም ሲሉ ተናግረዋል።
-መሠረት ሚድያ-



