በአባይ ግዮን ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም ላይ ዛሬ ጠዋት የድሮን ጥቃት ተፈፅሞ ምግብ ሲያዘጋጁ የነበሩ እናቶች መገደላቸው ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- በኢትዮጵያ በተለይም በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ምክንያት ንፁሀን ዜጎች፣ የሀይማኖት ተቋማት እና የሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት አሁንም ቀጥሏል።
ዛሬ ጠዋት 4፡30 አካባቢ በአባይ ግዮን ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም ላይ በመንግስት ሀይሎች በተፈፀመ እና አሰቃቂ ነበር በተባለ የድሮን ጥቃት ንፁሀን እናቶች ላይ ከባድ ጉዳት መድረሱን ምንጮች ከስፍራው ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
ይህ ድርጊት በሀገሪቱ ውስጥ በተለይም በቤተክርስቲያናት እና በገዳማት ላይ እያነጣጠሩ ያሉትን ተደጋጋሚ የድሮን ጥቃቶች አሳሳቢነት በድጋሚ አጉልቶ ያሳየ ክስተት የሆነ ሲሆን የአይን እማኞች ለሚድያችን ዛሬ ምሽት በስልክ እንደገለፁት ጥቃቱ ያነጣጠረው በገዳሙ ውስጥ "ቤተ-እግዚአብሔር" በመባል በሚጠራው እና እናቶች ለምዕመናን ምግብ ለማብሰል በሚጠቀሙበት ክፍል ላይ ነበር።
በዚህም ምክንያት የሰው ህይወት አልፏል፣ በርካቶች ቆስለዋል፣ እንዲሁም ህንፃው ሙሉ በሙሉ ፈርሷል ተብሏል።
በዚህ አሳዛኝ የድሮን ጥቃት ምክንያት አስራ ሶስት ንፁሀን እናቶች ጉዳት አስተናግደዋል። ከእነዚህም መካከል አንዲት እናት ጥቃቱ በተፈፀመበት ቅፅበት ወዲያውኑ ህይወታቸው ሲያልፍ ሌላኛዋ እናት ደግሞ ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላ በደረሰባቸው ከባድ ጉዳት ምክንያት ህይወታቸው አልፏል።
"ከሟቾቹ በተጨማሪ ሰባት ሰዎች ላይ ከባድ እና ቀላል የመቁሰል አደጋ ደርሷል። ከቆሰሉት መካከል አንደኛዋ ግለሰብ በህይወት እና በሞት መሀል እጅግ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ላይ ትገኛለች፣ ሌሎች ሶስት ሰዎች ደግሞ በህክምና ተቋም ውስጥ አስቸኳይ ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል" በማለት አንድ የጤና ባለሙያ የመረጃ ምንጫችን ተናግሯል።
"እነዚህ እናቶች በገዳሙ የተገኙት መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት እና ምግባረ ሰናይ ለማከናወን ነበር" የሚሉት በገዳሙ ያሉ አንድ አባት ናቸው።
የጥቃቱን ሁኔታ አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ "ዛሬ የቅዱስ ቂርቆስ ዝክር ስለነበር ምግብ ለማዘጋጀት ተሰባስበው የነበሩ 13 እናቶች እህል እየለቀሙ ነበር፣ በዚህ መሀል ነው በድሮን የተመቱት" በማለት የሁኔታውን አሳዛኝነት ገልፀዋል።
እናቶቹ ለዝክሩ የሚሆን እህል በማዘጋጀት ላይ የተፈፀመው ይህ የድሮን ጥቃት የቦታውን መንፈሳዊነት እና የሰዎቹን ንፁህነት ያላገናዘበ መሆኑን የገዳሙ አባቶች እና የአካባቢው ነዋሪዎች በሀዘን ይገልፃሉ።
ጥቃቱ በተፈፀመበት ሰዓት ምንም አይነት ወታደራዊ እንቅስቃሴ በገዳሙ አካባቢ አልነበረም የሚሉት እነዚህ በስፍራው ያሉ ምንጮች ናቸው።
የአካባቢው ነዋሪዎች እና ታዛቢዎች እንደሚያስረዱት ባለፈው አንድ አመት ጊዜ ውስጥ በስፍራው ላይ የፋኖ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ አልነበረም። መንገዶች በመዘጋጋታቸው ምክንያት አካባቢው በተወሰነ መልኩ ተነጥሎ የቆየ ሲሆን በቅርብ ርቀት ላይ የነበረው ብቸኛ የፀጥታ ሀይል የአድማ ብተና ካምፕ ብቻ ነበር ይላሉ።
ይህ ሁኔታ ጥቃቱ ለምን በገዳሙ እና በንፁሀን እናቶች ላይ ሊፈፀም ቻለ የሚለውን ጥያቄ ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል ተብሏል።
ምንም አይነት ወታደራዊ ስጋት በሌለበት፣ የታጠቁ ሀይሎች በማይንቀሳቀሱበት እና ንፁሀን ዜጎች ብቻ በሚገኙበት የሀይማኖት ስፍራ ላይ እንዲህ አይነት ከባድ የጦር መሳሪያ መጠቀም አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ህጎችን የሚጥስ ተግባር መሆኑን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በተደጋጋሚ ሲያነሱት የነበረ ጉዳይ ነው።
ይህ የአባይ ግዮን ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም ጥቃት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአማራ ክልል በቤተክርስቲያናት እና በንፁሀን ላይ እየደረሱ ካሉ ተከታታይ የድሮን ጥቃቶች አንዱ ነው።
እ.ኤ.አ. ከሚያዝያ 2023 ጀምሮ በመንግስት ሀይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ የመንግስት ሀይሎች ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮኖችን) በስፋት እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
በእነዚህ ጥቃቶች ምክንያት በፍኖተ ሰላም፣ በደንበጫ፣ በገደብ እና በሌሎችም በርካታ የአማራ ክልል ከተሞች እና የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ የገበያ ስፍራዎች፣ እና የሀይማኖት ተቋማት ኢላማ ሆነዋል። ለምሳሌ በፍኖተ ሰላም በተፈፀመ የድሮን ጥቃት በርካታ ንፁሀን መገደላቸው እንዲሁም በሌሎች አካባቢዎች ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት መውደማቸው ይታወሳል።
አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እና የአለም አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት (WCC) በመሳሰሉ ተቋማት በኩል በንፁሀን እና በሀይማኖት ስፍራዎች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ ተደጋጋሚ ጥሪዎች ሲቀርቡ ቆይተዋል።
በዛሬው ጥቃት የገዳሙ "ቤተ-እግዚአብሔር" ክፍል ሙሉ በሙሉ መውደሙ ታውቋል።
| መሠረት ሚድያ |


