ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን ፍልሰት የቀየረው የ66ቱ አብዮት
(መሠረት ሚድያ)- ቁጥሩ ይብዛም ይነስ ዛሬ በአሜሪካን ሀገር የትኛውም ማዕዘን ኢትዮጵያዊ አለ፣ በአንዳንድ የአሜሪካ ከተማዎች እና አካባቢዎች ኢትዮጵያውያን በብዛት ይታያሉ።
የኢትዮጵያ ምግቦች እና ቁሶች ንግድ የተጧጧፈባቸው፣ በሀገር ቋንቋ የሚነበቡ ማስታወቂያ የተለጠፉባቸው፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃ የሚደመጥባቸው ሌላም ሌላም ሀገር ቤትን የሚያስረሱ ትዕይንት የተስፋፉባቸው አካባቢዎች ሞልተዋል።
በተቃራኒው ለምልክት ያህል ጥቂት ኢትዮጵያውያን ብቻ ሚኖሩባቸው፣ የኢትዮጵያ ተቋማት ጨርሶ የማይታይባቸው አካባቢዎችም ብዙ ናቸው።
ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት ታሪኩ ሌላ ነበር። አንድ ኢትዮጵያዊ አሜሪካ የሚገኘው ወይ ለትምህርት አሊያም ዲፕሎማቲክ ሥራ ነው።
ታዲያ በጥቂት አስርት ዓመታት ውስጥ ታሪክ እንዴት ተቀየረ? ኢትዮጵያዊው እንዴት አሜሪካን ‘አጥለቀላቃት’? እንዴት ከአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያ በአሜሪካ የሚገኝ ሁለተኛው ትልቁ የዲያስፖራ ማህበረሰብ ሆነ?
ታሪኩን እንመልከተው!
አሜሪካ የቀረው የመጀመሪያው ስደተኛ ማን ነው?
የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ያነጋገራቸው በሴንትራል ሚችገን ዩኒቨርሲቲ የታሪከ ፕሮፌሰር የሆኑት ሰሎሞን አዲስ ኢትዮጵያውያን ወደ አሜሪካ ያላቸውን የፍልሰት እና ስደት ታሪክ የሚያትት ጥናታዊ መጸሐፍ አሳትመዋል፣ መጽሀፉም 'The History of Ethiopian Immigrants and Refugees in America, 1900-2000’ ይሰኛል።
እንደ እሳቸው ገለጻ በቀደመው ጊዜ በኢትዮጵያ ከሀገር ወጥቶ መቅረት እንደ 'ነውር' ይቆጠር ነበር።
“ለትምህርት ከሄዱ በኋላ ይመለሱ ነበር። እኔ [ለጥናታዊ ጽሁፍ] ካነጋገርኳቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ዲግሪያቸው ለመቀበል እንኳን በዚህ ሀገር አይቆዩም ነበር። ትምህርቱ እንዳለቀ ወደ ሀገር ቤት ይመለሳሉ። ዲግሪያቸው ለትምህርት ሚኒስቴር ይላካል” ይላሉ።
ቀጥለው ሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በመጣበት ጊዜ ንጉሡን ጨምሮ መኳንንቶቻቸው ሀገር ጥለው መሰደዳቸውን ካነሱ በኋላ ይህ ግን የተለየ የታሪክ ክስተት እንደሆነ ይገልጻሉ።
ከዚህ በተለየ ግን በዚያን ጊዜ በስደት መጥተው የቀሩ አንድ ሰው በታሪክ እንደሚጠቀሱ ፕሮፌሰሩ ያነሳሉ። እኚህ ሰው ዶክተር መላኩ በያን ይባላሉ።
“አሜሪካ መጥተው ቀሩ ከሚባሉት አንዱና ምናልባትም የመጀመሪያው ዶክተር መላኩ በያን ይባላል። እዚህ አሜሪካ ሀገር አፍሪካን አሜሪካዊት አግብቶ ይኖር የነበረ፣ ከዛም አሜሪካ ውስጥ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያን ድርጅት የመሠረተ ነው። በጣልያን ዘመን፣ ጣልያንን በመቃወም እና ፓንአፍሪካኒዝምን በማቀንቀን ምን አልባትም የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊ ዶክተር መላኩ ነበር” ይላሉ።
ዶክተር መላኩ አማኑኤል በያን ሃኪም፣ ዲፕሎማት፣ አርበኛ እና ፓንአፍሪካኒስት የሚል ቅጽሎች ነበሯቸው። በህክምና ሳይንስ ከሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ሲሆን ከአሜሪካ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ዲግሪ ያገኙ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ እንደሆኑ ይታመናል። በ1882 ዓ.ም የተወለዱት ዶክተር መላኩ ከአፍሪካዊ አሜሪካዊቷ ባለቤታቸው ዶሮቲ ሀድሊን አንድ ወንድ ልጅ ወልደዋል።
ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረበት ወቅት በተለይም የጥቁሮችን ድጋፍ ለማስተባበር በአውሮፓውያኑ 1937 የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን የሚል ተቋም መስርተው ነበር፣ Voice of Ethiopia የተሰኘ ጊዜጣም ያሳትሙ ነበር።
በአሜሪካ የመጀመሪያው ስደተኛ እንደሆኑ የሚታመኑት ግለሰብ በሳምባ ምች ምክንያት በአውሮፓውያኑ 1940 በኒውዮርክ ህይወታቸው አልፏል።
ከሳቸው ህልፈት ጥቂት አስርት ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያን መልክ ፍጹም የቀየረ አብዮት ፈነዳ። የፍንዳታው ትኩሳት የበርካታ ኢትዮጵያውያን ፍልሰት ጅማሮ ሆነ።
የ66ቱ አብዮት እና ስደት ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ
በየካቲት 1966 አብዮት በኢትዮጵያ ሲፈነዳ ስደት ጥዩፍ መሆኑም አብሮ አከተማ። ኢትዮጵያ እና ስደት ተዋወቁ። ፕሮፌሰር ሰለሞን “የኢትዮጵያ አብዮት ስደትን ለኢትዮጵያ ህዝብ አስተዋውቋል” ሲሉ ይናገራሉ።
ጥያቄው 'እንዴት?' የሚል ነው።
“አብዮቱ ሲመጣ እዚህ [አሜሪካ] የነበሩና አብዮቱን የሚደግፉት ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ። ጥርጣሬ የነበራቸው ግን እዚሁ ቀሩ። አሳይለም ጠየቀው መኖር ጀመሩ” ሲሉ ያክላሉ። አብዮቱ ጥቂት የማይባሉ ሰዎች ወደ ሀገራቸ መመለስ እንዲያመነቱ፣ እንዲፈሩ በዚያውም እንዲቀሩ አደርጓቸዋል።
ሀገር ቤት የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች “እሳቱን” ሸሽተው ባገኙት ቀዳዳ መሽሎክ ጀመሩ። ፕሮፌሰሩ፣ ብዙዎች ከሀገር እንዲሸሹ ያደርጓቸውን ምክንያት ሲሰነዝሩ የቀይ ሽብር እና ነጭ ሽብር መታወጅ ብሎም መሬት ለአራሹ የሚለው አዋጅ እንደ ምክንያት ያነሳሉ።
አዋጆቹ፣ ሰዎች አንድም ለህይወታቸው ፈርተው ሌላም የማያስተማምን ኢኮኖሚን ሰግተው አይናቸውን ወደ ውጪ እንዲያማትሩ አደረጋቸው።
ፕሮፌሰር ሰለሞን ሲናገሩ ሰዎች ከሀገር ሲሸሹ ሶማሊያን እንዲሁም “ገንዘብ ያላቸው” ጅቡቲን እንደመውጫ ቢጠቀሙም የሱዳንን ያህል ኢትዮጵያውያንን ያስተናገደ ሀገር የለም ይላሉ።
ሱዳን በርካታ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በበጎ እንደሚያነሷት የጠቀሱት የታሪክ ምሁሩ በወቅቱ ይፋ የሆነው ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያንን ወደ አሜሪካ የማስፈር መርሐ ግብር (resettlement program) ለበርካታ ኢትዮጵያውያን እፎይታ የሰጠ እንደሆነ ያነሳሉ።
ይህ ከመሆኑ ቀደም ብሎ ቀዳሚው ጆርጅ ቡሽ ወደ ሱዳን በመጓዝ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን መጎብኘታቸውን ፕሮፌሰሩ ይነሳሉ። በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ማርች 1985 በሮናልድ ሬጋን ዘመን ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩት ጆርጅ ቡሽ (ትልቁ) ለ72 ሰዓታት ሱዳንን እንደጎበኙ የዋይት ኋውስ መረጃ ያሳያል።
በዚህ ጉብኘት ወቀት የእርስ በእርስ ጦርነት እና ርሃብን ሸሽተው ሱዳን የተሰደዱ ሰዎችን እንደጎበኙ ተመዝገቧል። በዚህ ጉብኝታቸው የወቅቱን የኢትዮጵያ መንግስትን ክፉኛ የተቹ ሲሆን ችግሮችን ለመፍታት ሀገራቸው እንደምትሠራ ቃል ገብተዋል። ከዚህም በኋላ ከሱዳን በቻርተር አውሮፕላን የተወሰዱ የተወሰኑ ስደተኞች እንደነበሩ የጠቁሰት ፕሮፌሰር ሰለሞን ለዚህ ሶስት ምክንያት እንዳለ ያስረዳሉ።
የመጀመሪያው በሰብአዊነት ኢትዮጵያውያኑን ለመታደግ የተደረገ ነው ብለዋል። ቀጥሎም አንዳንዶቹ ስደተኞቹ “አሜሪካ የተማሩና ጸረ አብዮት ተብለው” የተፈረጁ እንደነበር ጠቅሰው “ኢንቨስት ያደረገችባቸው ሰዎች” እንዳይባክኑ በሚል ነው። ሦስተኛው ደግሞ እነዚህ ተማሪዎች ከሀገራቸው ከወጡ እና ዳግም ካልተመለሱ ኮሚኒዝም በኢትዮጵያ ይደከማል በሚል ስሌት እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ለዚህ ነው ያኔ “ሱዳን መግባት አሜሪካ ለመግባት ዋስትና “ ተደርጎ የሚወሰደው የሚሉት። በዚህ ሳቢያ ሱዳን የነበረውን “ሪሴትልመንት” ለመጠቀም በርካታ ኢትዮጵያውን ወደ ሱዳን ሲሰደዱ ነበር።
እነዚህ ስደተኞች ደግሞ “አንዴ አሜሪካ ከገቡ በኋላ ”በ chain migration [አንዱ ሌላኛውን በመሳብ] ቤተሰቦቹን በቪዛ ያመጣል” ብለዋል። ይህ ሁኔታ እየተስፋፋ መጥቶ በአሜሪካ፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ከናይጄሪያ ቀጥሎ ሁለተኛው ስደተኛና የዲያስፖራ ቁጥር ያላት ሀገር እንደትሆን አድርጓል ይላሉ ፕሮፌሰር ሰለሞን።
“በአሁኑ ስታቲክስ ወደ 300 ሺህ ኢትዮጵያዊ አሜሪካ ውስጥ አለ” ሲሉም አክለዋል።
ስደተኞቹ እንዴት ይሰፍራሉ?
ኢትዮጵያውን ወደ አሜሪካ ያደረጉትን ስደት በተመለከተ ጥናት የሰሩት ፕሮፈሰር ሰለሞን አሜሪካ ስደተኞቹን “ዝም ብላ የሆነ ቦታ አታሰፈርም” ሲሉ ያስረዳሉ።
“የዘር ተዋጾን፣ የስነልቦና ግንዛቤን እና labor demand (የሥራተኛ ፍላጎት) ያለበት ቦታን ተመልክተው ሪሴትል የሚያደርጉት” ሲሉ አክለዋል።
የዘር ተዋጾ ሲባል አፍሪካ አሜሪካውያን በቁጥር አነስተኛ በሆኑባቸው አካባቢዎች ኢትዮጵያውያን እንዲሰፈሩ መደረጉን እንደምሳሌ ያነሳሉ። መጀመሪያ አካባቢ ከሱዳን የመጡ ወደ 11 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ካሊፎርንያ ነበር የሰፈሩት።
አሜሪካ የስደተኞች ሀገር ናት የሚሉት ፕሮፌሰሩ “እነሱም ይህንን ያውቃሉ፣ አዲስ የሚሰራ ህዝብ እስካለ እድገት አለ” ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ውስጥ ከወንጀል ጋር መሰል ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ስማቸው እንደማይነሳ ያብራራሉ። ይህ ስመ ጥር በሆኑ አሜሪካውያን ጨምር የተመሰከረ እንደሆነ አንስተዋል።
በእዮብ ሞገስ ለመሠረት ሚድያ
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።-መሠረት ሚድያ-





