የእነ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው እና አቶ ክርስቲያን ታደለ የምስክር አሰማም ሂደት ለጊዜው ታግዶ እንዲቆይ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ
(መሠረት ሚድያ)- ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዙን የሰጠው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ- ሽብር እና የሕግ- መንግሥትዊ ጉዳዮች ችሎት አንድ የአቃቤ ሕግ ምስክር ከመጋረጃ ጀርባ ሊመሰክር ይገባል የሚለውን የፈቃቤ ሕግ መከራከሪያን ተቀብሎ ብይን በመስጠቱ ምክንያት ተከሳሾቹ ይግባኝ በመጠየቃቸው ነው።
የተከሳሽ ጠበቆች በይግባኙ አቤቱታ ላይ እንደገለፁት አቃቤ ሕግ 15 ምስክሮችን ካሰማ በኋላ ቀድሞ በስም ዝርዝሩ ውስጥ ያልተካተተን ምስክር በመጋረጃ ጀርባ እንዲመሰክር ብሎ ማቅረቡ የተከሳሾችን መብት በእጅጉ የሚጎዳ በመሆኑ ይሄው የስር ፍርድ ቤቱ ብይን ሊነሳ ይገባል የሚል ነው።
በዚህም መሰረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተከሳሾችን ይግባኝ መርምሮ ብይን እስኪሰጥበት ድረስ የስር ፍርድ ቤቱ የጀመረውን ምስክሮችን የመስማት ሂደት ለጊዜው አግዶ እንዲቆይ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በጉዳዩ ላይ አቃቤ ህግ መልሱን እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2017 ዓ/ም ድረስ እንዲያቀርብ ታዟል።
በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው መዝገብ ስር አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ዶ/ር ካሳ ተሻገር፣ ዶ/ር ጫኔ ከበደ፣ ቄስ በላይ አዳሙ እና ሌሎቹም ይገኛሉ።
መረጃን ከመሠረት!



