ኢትዮ ቴሌኮም ለሰራተኞቹ አመታዊ የደሞዝ ጭማሪ ይፋ አደረገ፣ ሰራተኞች በበኩላቸው የጭማሪው መጠንን ማነስ ተቃውመው እንደማይቀበሉት እየገለፁ ነው
(መሠረት ሚድያ)- ኢትዮ ቴሌኮም የ2017 ዓ.ም የበጀት ዓመት የስራ አፈጻጸሙን መሰረት በማድረግ አመታዊ የደመወዝ ጭማሪ ባሳለፍነው ቅዳሜ ነሐሴ 17 ቀን 2017 ዓ.ም ማፅደቁ ታውቋል።
በበጀት ዓመቱ የተከናወነው የውጪ ምንዛሪ ለውጡ ተቋሙ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማድረጉን የጠቆመው ተቋሙ ችግሩን ለመቋቋም ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ቢሆንም ትርፋማነቱ ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ አልቀረም ብሏል።
"የተመዘገበውን አመርቂ ውጤት ተከትሎ የበጀት አመቱን የስራ አፈፃጸም እና ትርፋማነትን መሰረት በማድረግ አመታዊ የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ በህብረት ስምምነቱ መሰረት የሰራተኛ ማህበር ተወካዮች ከማኔጅመንት ጋር በመግባባት መንፈስ የጋራ አላማንና የተቋም ቀጣይነትን ታሳቢ አድርጎ ድርድር ተካሂዷል" በማለት ኢትዮ ቴሌኮም ያወጣውና መሠረት ሚድያ የተመለከተው ሰነድ ያሳያል።
አክሎም "ድርድሩ ሲከናወን የተቋሙን ትርፋማነትና የመክፈል አቅም እንዲሁም የኩባንያውን የገንዘብ ፍሰት እና የማክሮ ኢኮኖሚክ ሪፎርሙን ተከትሎ የተከሰተው የውጭ ምንዛሪ ኪሳራ በኩባንያችን ትርፋማነት ላይ ያሳደረውን ጫና እንዲሁም አሁናዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ ነው" ይላል።
በዚህም መሰረት የደሞዝ ጫማሪው በተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ ለስራ አመራር ቦርድ ቅዳሜ ነሐሴ 17 ቀን 2017 ዓ.ም ቀርቦ እና ውይይት ተደርጎ የጸደቀ እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን ጭማሪው አነስተኛ ደመወዝ ያላቸውን ሰራተኞች ተጠቃሚነትን ታሳቢ ያደረገ ሆኖ አጠቃላይ የጭማሪው መጠን 17 ፐርሰንት እንዲሆን ተወስኗል ይላል።
ይሁንና የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞች የጭማሪ መጠኑን ተቃውመው ማኔጅመንቱን ክፉኛ እየወቀሱ ይገኛሉ።
"ድሮ የተቋሙ አመታዊ የደሞዝ ጭማሪ አነሰ ቢባል 24 ፐርሰንት፣ በዛ ቢባል 30 ፐርሰንት ነበር። ዛሬ ግን የዋጋ ግሽበቱ ጣሪያ በነካበት ዘመን የ17 ፐርሰንት በሽታ በየመቱ እያሰቃየን ነው" በማለት አንድ የተቋሙ ሰራተኛ ተናግረዋል።
እንደ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና አየር መንገድ ያሉ የሰራተኛ ተቋሟት ከማኔጅመንት ጋር በመነጋገር የተሻለ ጥቅማጥቅም ለሰራተኛ እንደሚያስገኙ የሚገልፁት የኢትዮ ቴሌኮም ሰራተኞች የራሳቸውን ተወካዮችም ኮንነዋል።
"የትራንስፖርት እና የቤት ጉዳይ እንዴት ነው? እንደ አብርሃም በዳስ፣ እንደማጅላን በእግር ብቻ የምንጠቀም ነው የሚመስላቸው። ታክስ 1 ብር፣ ቤት ኪራይ 500 ብር በነበረበት ጊዜ እንዳለ ነው የሚመስላቸው? ነው ወይስ ለእያንዳንዳችን የቤት ባለቤትና የመኪና ባለቤት ያደረጉን ይመስላቸዋል?" በማለት ሰራተኞቹ ይጠይቃሉ።
እነዚህ ለሚድያችን ቅሬታ ያቀረቡ ሰራተኞች ተቋሙ ላይ በተሰራው ረቂቅ የሂሳብ ሪፖርት መሰረት አጠቃላይ 162 ቢሊዮን ብር ገቢ በማስገኘት የእቅዱን 99 ፐርሰንትአሳክቷል ይላሉ።
በበጀት አመቱ የተገኘው ገቢ ካለፈው በጀት አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም በ72.9 ፐርሰንት እድገት እንዳሳየ ይጠቁማሉ።
"በዓመቱ 2.38 ትሪሊዮን ብር የኤሌክትሮኒክ ገንዘብ ዝውውር በቴሌ ብር በማከናወን የእቅዱን 116.9% ያሳካ ሲሆን አጠቃላይ አመታዊ የግብይት መጠኑ (Transaction Volume) 1.06 ቢሊዮን ነው፡፡ አገልግሎቱ ከተጀመረ ጀምሮ አጠቃላይ በኢኮኖሚው ውስጥ 4.93 ትሪሊየን ብር የኤሌክትሮኒክ ገንዘብማንቀሳቀስ የተቻለ ሲሆን አጠቃላይ የአራት አመታት የግብይት መጠኑ 1.98 ቢሊዮን ነው" በማለት ተቋሙ በሰራተኞቹ ጥረት ማሳካት የቻለውን ያስረዳሉ።
ይሁንና አሁን ይፋ የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ ይህን የተቃሙን ስኬት እንደማያመላክት በመጥቀስ ቅሬታቸውን ለዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በፅሁፍ በትናንትናው እለት ማስገባታቸው ታውቋል።
-መሠረት ሚድያ-




