በዛሬው ዕለት በምስራቅ አርሲ ዞን ልዩ ቦታው ጠለታ ቅዱስ ገብርኤል በተባለ አካባቢ ሶስት ምዕመመናን መገደላቸው ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- አርሲ ዞን ውስጥ የምዕመናን ግድያ እና የወጣቶች አፈና አሁንም ተባብሶ እንደቀጠለ የታወቀ ሲሆን በዛሬው ዕለትም ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ገደማ በዞኑ ልዩ ቦታው ጠለታ ቅዱስ ገብርኤል በተባለ አካባቢ አውድማ ላይ እህል እየወቁ የነበሩ ሶስት ሰዎች በጥይት ተመተው መገደላቸው ታውቋል።
የማህበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን የአካባቢው ነዋሪዎችን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ከተገደሉት ምእመናን መካከል ዲ/ን ኢዮብ እጅጉ፣ ጥላሁን ቦጌ እና ሕፃን ጻድቃኔ ሠራዊቱ የተባሉ የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ይገኙበታል።
ሥርአተ ቀብራቸው በጠለታ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በዛሬው ዕለት ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ላይ ተፈፅሟል።
በተጨማሪም ከዚህ ቀደም በነበሩ የምዕመናን አፈናና ግድያን በተመለከተ መረጃ አቀብላችኋል በሚል ምክንያት የአካባቢው ወጣቶች ወዳልታወቀ ሥፍራ ታስረው እየተወሰዱ እንደሚገኝ ነዋሪዎቹ ለማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ተናግረዋል።
"በሥፍራው ላይ የጸጥታ ሀይል ቢኖርም ኢ-ሰብአዊ ድርጊቱ፣ አፈናና ግድያውም ተባብሶ መቀጠሉን ቀጥሏል" ብለው ለማህበረ ቅዱሳን ቴሌቭዥን የተናገሩት ምዕመናኑ ናቸው።
"ስለጉዳዩ ተጨማሪ መረጃ ለመጠየቅ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መዋቅር ወደ ሆነው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ እና የዞኑ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ የእጅ ስልክ ላይ በተደጋጋሚ ብንደውልም ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል" በማለት መረጃውን አጋርቷል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ሰዓት ሴቶች እና ሕጻናት አካባቢውን ለቀው ወደ ሌላ ቦታም እየሸሹ እንደሆነም ታውቋል።
የአሁኑን ጨምሮ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ብቻ በተፈፀሙ አራት ተከታታይ ጥቃቶች 28 ሰላማዊ ሰዎች ግድያ እንደተፈፀመባቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
በምሥራቅ አርሲ ሀገረ ስብከት በሆንቆሌ ዋቤ ወረዳ በቀቅሳ ቀበሌ ጥቅምት 18 ለ19 አጥቢያ ከምሽቱ 4፡00 ላይ አምስት ምእመናን በታጣቂዎች መገደላቸው ተዘግቦ ነበር።
በተመሳሳይ ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ከለሊቱ 4 ሰዓት አካባቢ በምሥራቅ አርሲ ሽርካ ወረዳ ሄላ ዘባባ ቀበሌ አርሴማ አጥቢያ የሚኖሩ ምእመናን በታጠቁ ኃይሎች በአሰቃቂ ሁኔታ ሦስቱ መገደላቸው እና አራቱ ደግሞ መታገታቸው ተገልጿል።
በሶስተኛነት በአርሲ ሀገረ ስብከት ጉና ወረዳ በሚገኘ ኖኖ ጃዊ ቀበሌ የሚኖሩ 14 ምዕመናን ከለሊቱ 6 ሰዓት አካባቢ በዕለተ ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2018 ዓ.ም ለ14 አጥቢያ ከተኙበት ከቤታቸው አስወጥተው የታጠቁ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሲሆን ስድስቱ ከመገደላቸው ከአንድ ቀን በፈት ቀድመው ታፍነው ተወስደው ነበር ተብሏል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ማለትም ከ2016 ዓ.ም መስከረም 02 ጀምሮ እስከ 2017 ዓ.ም ድረስ ያለማቋረጥ በወረዳው ከ115 በላይ ምእመናን የተገደሉ ሲሆን 27 ምዕመናን ደግሞ አሁንም ድረስ ታግተው ያሉበት እንደማይታወቅ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በወረዳው ካሉ 37 አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ከ16 በላይ የሆኑት አገልግሎት የማይሰጡ መሆናቸውንና ከእነዚህም መካከል 3ቱ ሙሉ በሙሉ መዘረፋቸውን ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል በአርሲ ዞን የተከሰተውን ችግር እንዲያጣራ የተሰየመው የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ኮሚቴ መግለጫ አነጋጋሪ ሆኗል።
ዛሬ የመጀመሪያ ደረጃ ነው የተባለ ሪፖርቱን ያወጣው ኮሚቴው በወረዳዎቹ የሰዎች መገደል፣ መታጋት እና የንብረት ውድመት መከሰቱን ከአካባቢው ማሕበረሰብና ጉዳት ከደረሰባቸው ወገኖች መረጃ ማግኘቱን ጠቅሶ የተገደሉት ሰዎች እንዲሁም የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ያጋጠማቸው ዜጎች የአንድ የሃይማኖት ተከታይ እና አገልጋዮች አለመሆናቸውን አንስቷል።
ይሁንና በርካታ ዜጎች ሪፖርቱ የድርጊቱን ሰለባዎች በትክክል ከመለየት እና መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ የመሸፋፈን ስራ እንደሰራ በመግለፅ ሀሳባቸውን ማህበራዊ ሚድያ ላይ እያጋሩ ይገኛሉ።
መሠረት ሚድያ በዚህ ዙርያ ሰፋ ያለ የምርመራ ዘገባ በመስራት በቅርቡ ለህዝብ ያደርሳል።
-መሠረት ሚድያ-





