ለ64 ዓመታት ስራ ላይ የዋለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ በነገው እለት በፓርላማ ተሽሮ በአዲስ ሊቀየር መሆኑ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት በ1954 ዓ.ም ስራ ላይ ውሎ የነበረው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርዓት ሕግ በነገው ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሽሮ በምትኩ “የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ” በሚል አዳዲስ የሥነ-ሥርዓት ሕግጋትን ባካተተ ሕግ ስራ ላይ ሊውል መሆኑን መሠረት ሚድያ ሰምቷል።
አዲሱ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እየተንከባለለ መቆየቱን የጠቆሙት ምንጮች በቀድሞው ሥነ-ሥርዓት ሕግ ያልተሸፈኑ በርካታ ሕጎች ተካተውበታል ብለዋል።
የሥነ-ሥርዓት ሕጉ አላማም ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እና ሀገሪቱ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር ለማጣጣም የታለመ ነውም ተብሏል።
የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ በ1996 ዓ.ም ሲሻሻል የሥነ-ሥርዓት ሕጉ አብሮ መሻሻል አለበት በሚል በወቅቱ ክርክር ተነስቶበት የነበረ ሲሆን ከ64 ዓመታት በኋላ ነገ የካቲት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ ሕግ ሊተካ ሰዓታት ቀርተውታል።
የሥነ ሥርዓት ሕጉ ብዙ አዎንታዊ ጎኖች ቢኖሩትም ከፋፋይ ነው በሚል በፓርላማ አባላት ዘንድ ከፍተኛ ክርክር ሲያስነሳ ቆይቷል። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ በአዲስ አበባ በሚገኙ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ንብረቶችን ለመጠበቅ በሚል የቀረቡ አንቀጾች ይገኙበታል።
ክርክከሩ እየሰፋ እና እየከረረ በመሄዱ ለበርካታ ግዜያት ለሕግ እና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ከዚያም ከፍ ሲል ለጠቅላላ ጉባኤው እየቀረበ ሲያጨቃጭቅ ዓመታትን ፈጅቷል።
አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንኑ የሥነ-ሥርዓት ሕግ ለማፅደቅ ተስኖት ለስደስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳልፎ ሰጥቶ ነበር።
አሁን ላይ ያለው ምክር ቤት በስራ ዘመኑ መጠናቀቂያ አዲሱን ሕጉን አፅድቆ እንደሚበተን ታውቋል።
-መሠረት ሚድያ-


