አክቲቪስት ስዩም ተሾመ በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት ቀርቦ ተመክሮ ተለቀቀ
(መሠረት ሚድያ)- ሚድያችን ከሰሞኑ በተከታታይ ሲያቀርባቸው በነበሩ ዘገባዎቹ የፌደራል ፖሊስ ለፍርድ ቤት በፃፈው ደብዳቤ አክቲቪስት ስዩም ተሾመ የተባለ ግለሰብን ፈልጎ ማግኘት እንዳልቻለ መግለፁን ጠቁሞ ነበር።
አክቲቪስቱ በሕግ ቁጥጥር ስር ሆነን ሳለ ስማችንን በማጥፋት ብሎም በፍርድ ቤቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው በሚል አቶ ዮሐንስ ቧያሌውና አቶ ክርስቲያን ታደለ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ማመልከታቸው ይታወቃል።
የሁለቱ አመልካቾችን የክስ መዝገብ የሚመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ስዩም ተሾመ የተባለው ግለሰብ የተከሳሾቹን ክብርና ዝና አጉድፏል፣ ችሎቱንም በሚዲያ ደፍሯል በሚል ከስድስት ጊዜ በላይ መጥሪያ ተልኮ ሳይገኝ ቀርቷል።
ይሄው ግለሰብ በዛሬው ዕለት በዳኞች ቢሮ ተገኝቶ ጉዳዩን የሚመለከቱት ዳኞች ዳግመኛ እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ ድርጊት እንዳትፈፅም ብለድ በምክር አልፈውታል።
አቶ ዮሐንስ ቧያሌው እና ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው ጉዳዩ መታየት ያለበት በግልፅ ችሎት እንጂ በጓሮ መሆን የለበትም ሲሉ የተከራከሩ ቢሆንም ዳኞቹ ነገሩን ቀለል ለማድረግ በቢሮ ይሻላል በሚል ሁለቱን ለማስታረቅ ጥረት ማድረጋቸውን የመሠረት ሚዲያ ምንጮች ገልፀዋል።
“ዛሬ ስዩምን የጠራነው ልናስረው ሳይሆን ልንመክረው እና ከእናንተ ጋር ልናስታርቃችሁ ነው”
አቶ ዮሐንስ ቧያሌው ከአራት አመት በፊት አቶ ስዩም ስሜን በማጥፋት እና ጉዳዩን ሲመለከተው የነበረውን ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል አራት ወር እና መቶ ሺህ ብር ካሳ እንዲከፍል ችሎት የበየነበት ቢሆንም እስካሁን ቅጣቱ ሊፈፀም አልቻለም፣ ስለሆነም ፖሊስ አክቲቪስቱን ፈልጎ ቅጣቱን እንዲያስፈፅም ፍርድ ቤቱ የፃፈው ትዕዛዝ እጄ ላይ ስላለ ይሄ ፍርድ ቤት ያስፈፅምልኝ ሲሉ የትዕዛዙን ደብዳቤ ለችሎቱ አሳይተዋል።
ችሎቱ በበኩሉ 'ዛሬ ስዩምን የጠራነው ልናስረው ሳይሆን ልንመክረው እና ከእናንተ ጋር ልናስታርቃችሁ ነው' ማለታቸውን የመሠረት ሚዲያ ምንጮች ጠቁመዋል።
አክቲቪስቱ በዳኞች ከተመከረ በኋላ ፌደራል ፖሊስ አጅቦት ከፍርድ ቤቱ ግቢ መውጣቱን መሸኘቱን በስፍራው የነበሩ ምንጮች አረጋግጠዋል።
መረጃን ከመሠረት!




በዳይም ፈራጅም አንድ ሰው።