በጋምቤላ ክልል በተከሰተው አደገኛ ግጭት ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው ታወቀ
(መሠረት)- ጋምቤላ ክልል ውስጥ በመዲናዋ ጋምቤላ ከተማ፣ በአቦል፣ በተርፋም እና ኢታንግ ወረዳዎች እንዲሁም ዛሬ በሌሎች አዋሳኝ ወረዳዎች እጅግ ከፍተኛ የሆነ ደም አፋሳሽ ግጭት እየተካሄደ መሆኑን በስፍራው ያሉ ምንጮቻችን እየተናገሩ ይገኛሉ።
የብሄር መልክ በያዘው እና በተለይ በኑዌር እና በአኙዋክ መሀል እየተካረረ የመጣው ግጭት የበርካታ ሰዎችን ህይወት ከመቅጠፉም በላይ የፌደራሉ መንግስት በአስቸኳይ ጣልቃ ካልገባ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት አደጋ ላይ እንዳለ ሰምተናል።
ግጭቱ በተለይ ባሳለፍነው ማክሰኞ የጋምቤላ ፖሊስ አዛዥ የሆኑት ኦሞድ ፑዋል ኦጁሉ ቢራቸው በር ላይ ከተገደሉ በኋላ መባባሱ ታውቋል።
ከከተማው ውጊያ በተጨማሪ ቡርቤ ከተባለው የመተሃር ቀበሌ (ከደቡብ ሱዳን ጋር የሚዋሰን የመጨረሻ የኢትዮጵያ ቀበሌ) አንስቶ እስከ ተርፋም ድረስ የተሰባሰቡ የኑዌር ብሄር ተወላጆች አቦል የተባለ የአኙዋኮችን ቀበሌ ለማጥቃት እየተመሙ እንደሚገኙ ታውቋል።
አንድ በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የሆስፒታል ምንጭ ከ200 በላይ ሰዎች መሞታቸውን እንደሰሙ፣ በርካታ ሰዎችም ህይወታቸው አልፎ እና ተጎድተው ወደ ሆስፒታሉ እንደመጡ ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
"በጥይት፣ ገጀራ እና ስለት ባለው ነገር የተጎዶ በርካቶች ናቸው። አሁን ላይ ከእኛ አቅም በላይ ሆኗል" ያሉት የጤና ባለሙያው ናቸው።
አንድ የከተማው ነዋሪ በየመንገዱ የተበታተኑ አስከሬኖች እስከ ዛሬ ከሰዓት ድረስ ይታይ እንደነበር ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ጋምቤላ ከደምቢዶሎ 100 ኪሎሜትር ገደማ ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (መንግስት ሸኔ የሚለው) በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛሉ የተባለ ሲሆን ከአካባቢው መከላከያ ተጠራርጎ ከወጣ ቆይቷል ተብሏል።
"በአጠቃላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን ለማስቀመጥ ባይቻልም የአሁኑ ግጭት ተራ ግጭት ከመሆን ወደ ጦርነት ከመሻገሩም በላይ የፖለቲከኞቹ እጅ አለበት።በቅርቡ በነበራቸው ስብሰባ በተለይ የኑዌር ፖለቲከኞች ምክትል ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ ስብሰባ ረግጠው ወጥተው ነበር" የሚሉት አንድ የመረጃ ምንጫችን የኑዌርና አኙዋክ ግጭት የቆየና ብዙ ውስብስብ ምክንያት ያለው ነው ይላሉ።
"የቅርቡን ለማስቀመጥ ያክል አቦል የሚባል የአኙዋክ ወረዳ አካባቢ ኑዌሮችን እና ሌሎች ነዋሪዎችን በጫኑ ተሽከርካሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ደረሱ፣ የሰዎች ህይወትም አለፈ። ከዛም ተርፋም የተባለ የኑዌሮች አካባቢ የሚሰሩ አኙዋኮች በመልሶ ማጥቃት ተገደሉ፣ ከዛም ጋምቤላ ዋና አደባባይ አካባቢ ሁለት የአቢሲንያ ባንክ ባልደረባ የኑዌር ተወላጆች በጥይት ተገደሉ" በማለት የተከሰተውን አስረድተዋል።
አክለውም "ማክሰኞ ደግሞ ኮማንደር ኡሞድ የተባለ የአኙዋክ ተወላጅ የጋምቤላ ከተማ የፖሊስ አዛዥ ቢሮው በር ላይ በኑዌር ታጣቂዎች ተገደለ። ከዛች ሰዐት ጀምሮ በተለየዩ ቦታዎች ውጊያዎች እየተደረገ ነው፣ በተለይ ከጋምቤላ ወደ ላሬ መውጪያ በተለምዶ የኑዌር ብሔር ብሔረሰብ የሚባል ቦታ ውጊያ እየተደረገ ነው" በማለት ለሚድያችን ተናግረዋል።
አንድ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ "ግጭቱ ከመጀመሪያውም የብሔር ግጭት ነው። በዋናነት የአኙዋክና የኑዌር ግጭት ቢሆንም ጸያይም መልክ ያለው በተለምዶ ሀበሻ (ቡኝ) በመባል የሚታወቀው ማህበረሰብም የሞትም ፣ የመቁሰልም ፣ የመዘረፍ አደጋ ገጥሞታል" ይላሉ።
አቦል ከጋምቤላ 18 ኪሎሜትር ላይ የሚገኝ ሲሆን ከሁለቱም ወገን ከፍተኛ እልቂትና ጥፋት መድረሱ ይነገራል። ኑዌር የቁጥር የበላይነት ቢኖራቸውም ሁለቱም ወገን በከፍተኛ ደረጃ እንደታጠቁ መረጃዎች ያሳያሉ።
ከዚህም በተጨማሪ እንደ ፌስቡክ ያሉ የማህበራዊ ሚድያዎችን በመጠቀም ግጭቱን ለማስፋፋት እየተሞከረ እንደሆነ ታዝበናል።
የኑዌር ታጣቂ በተለይ 'አጉል ንያንግ' በተባለ ቦታ እጅግ ከፍተኛ ጥቃት አድርሰው በርካቶች ማለቃቸው ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪ የደቡብ ሱዳን አማፂ ቡድን (SPLM-IO) አባላት ድንበር አቋርጠው በመግባት የአኙዋክ ብሄርን እያጠቁ እንደሚገኙ ታውቋል።
"የፌደራል መንግስት የት አለ? ግጭቱ ዛሬም ከነጋ በተለያዩ ቦታዎች የቀጠለ ሲሆን ከተራው ማህበረሰብ በእኩል ደረጃ የየብሔረሰብ ታጣቂዎች የኔ ከሚሉት ጎን ቆመው እየተዋጉ ናቸው። ዛሬ በተለይ ጋምቤላ ውስጥና ኢታንግ የተባለው አካባቢ ከፍተኛ ውጊያ እየተደረገ ይገኛል" ያሉት አንድ የአካባቢው ምንጭ ናቸው።
የፌደራል መንግስት እስካሁን በደም አፋሳሹ ግጭት ያለው ነገር ባይኖርም የጋምቤላ ክልል ትናንት ባወጣው መግለጫው የፀጥታ ስራ ከሚሰሩ አባላት ውጪ የትኛውንም የጦር መሳሪያ ይዞ የሚገኝ እና የሚንቀሳቀስ ግለሰብ ወይም ቡድን ላይ አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ አስጠንቅቋል።
-መሠረት ሚድያ-




