'ወደ ሕክምና ውሰዱኝ' በማለት ሲማፀኑ የነበሩ አንድ የ63 አመት አዛውንት በዛሬው እለት በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- አቶ አባይነህ አለማየሁ የተባሉት እኚህ የ63 ዓመት አዛውንት ከባህር ዳር ከተማ ወንድማቸውን ለመጠየቅ ነበር ወደ አዲስ አበባ የመጡት።
አዲስ አበባ እንደገቡ ግን 'ከፋኖ ታጣቂዎች ተልዕኮ ተቀበለህ መጥተሀል' በሚል ጥርጣሬ ለአራት ወራት ያህል በእስር ላይ ቆይተው እንደነበር የደረሰን ማስረጃ ያሳያል።
ይሁንና እስረኛው ዛሬ ሕይወታቸው ማለፉን እና ምክንያቱም በህክምና እጦት ምክንያት መሆኑን ምንጮቻችን ለመሠረት ሚዲያ ገልፀዋል።
አቶ አባይነህ በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ በምርመራ በቆዩበት ወቅት በድብደባ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ችሎት ቀርበው የተናገሩ ቢሆንም በቂ ሕክምና ሳያገኙ ቆይተዋል ሲሉ የገለፁት ምንጮች ጉዳቱ በጊዜ ሂደት አመርቅዞ ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል ብለዋል።
የግለሰቡን ህልፈት ቤተሰቦችም አረጋግጠዋል።
በዛሬው ዕለት በማረሚያ ቤት ውስጥ ሕይወታቸው ያለፈው አቶ አባይነህ 'ህመም እየተሰማኝ ነው፣ ወደ ሕክምና ውሰዱኝ' ቢሉም 'አጃቢ የለም' በሚል ሕክምና ሳያገኙ መዋላቸውን ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ አንድ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ባልደረባ ለመሠረት ሚዲያ ተናግረዋል።
አቶ አባይነህ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ የሽብር ወንጀል ችሎት በ40 ሺህ ብር ዋስ እንዲፈቱ የበየነ ቢሆንም ፌደራል ፖሊስ በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተማ ሽብር ለመፍጠር ሲያሴሩ አግኝቻቸዋለሁ በሚል ሌላ ክስ ከፍቶ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ማድረጉ ታውቋል።
ይሄው ፍርድ ቤት በሁለተኛውም ክስ በሠላሳ ሺህ ብር ዋስ ውጭ ሆነው እንዲከራከሩ ቢበይንም ሳይለቀቁ መቆየታቸውን እና በዚህ መሀል በምርመራ ወቅት በደረሰባቸው ደብደባ ምክንያት እና በህክምና እጦት በማረሚያ ቤት ውስጥ ሕይወታቸው ማለፉን ሚዲያችን አረጋግጧል።
መረጃን ከመሠረት!



