ዛሬ በሰሜን ወሎ በአንድ ጤና ጣቢያ ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት ሦስት ሰዎች ሲገደሉ ሁለት የጤና ባለሙያዎች መቁሰላቸው ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- በሰሜን ወሎ ዞን ጉባላፍቶ ወረዳ ሳንቃ ጌሾ በር ጤና ጣቢያ ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት የሦስት ሰዎች ሕይወት ወዲያውኑ ሲያልፍ ሁለት የጤና ባለሙያዎች ደግሞ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ወልድያ ሆስፒታል መላካቸውን አንድ የሳንቃ ከተማ ነዋሪ ለመሠረት ሚዲያ ተናግረዋል።
የዓይን እማኙ እንደገለፁት ዛሬ ቅዳሜ (መስከረም 17 ቀን 2018 ዓ/ም) ከቀኑ 6:00 ሰዓት ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት ልጃቸውን ለማሳከም የተገኙ አባት እና እናት ከእነ ልጃቸው ሕይወታቸው ሲያልፍ ሁለት የጤና ባለሙያዎች ደግሞ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ እያሉ ከባድ ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲሉ ገልፀዋል።
ሁለቱን የጤና ባለሙያዎች ከፍርስራሹ ውስጥ ያነሳኋቸው እኔ ነኝ ያሉ ሌላው የዓይን እማኝ "የለበሱት ጋውን በደም ተነክሮ ነው ያገኘኋቸው" ይላሉ።
"ለማሳከም የመጡት አባት እና እናት ልጃቸውን ጨምሮ ሳገኛቸው ሕይወት አልነበራቸውም" ሲሉ አክለዋል።
በጉባላፍቶ ወረዳ ስር የምትገኘው ሳንቃ ጌሾበር ከወልድያ ወደ ባሕርዳር መስመር አቅጣጫ 23 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
ሰሞኑን በሰሜን ወሎ ዞን መቀመጫ ወልድያ ከተማ አቅራቢያ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ መኖሩን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመላክታል።
በተመሳሳይ በወልድያ ዙሪያ ሲሪንቃ፣ መርሳ፣ ጊራና በሚባሉ አካባቢዎች በሁለቱ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጥ መኖሩን የአካባቢው ነዋሪዎች ለመሠረት ሚዲያ ጠቁመዋል።
-መሠረት ሚድያ-



