ሰሜን ወሎ በሚገኘው ጃራ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ላይ በደረሰ ጥቃት የበርካታ ሰው ህይወት መጥፋቱ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ትናንት መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት በሰሜን ወሎ ዞን ሐብሩ ወረዳ እና በአፋር ክልል ጭፍራ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢ 'ጃራ' ተብሎ በሚጠራው የወታደር ማሰልጠኛ ጣቢያ ላይ ድንገተኛ ተኩስ ተከፍቶ በርካታ ምልምል የሚሊሻ አባላት ህይወታቸውን ማጣታቸው እና ሌሎቹ መቁሰላቸውን የዓይን እማኞች ተናገሩ።
ጥቃቱን የፈፀሙት በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ታጣቂዎች ሳይሆኑ አይቀርም ብለው የመረጃ ምንጮች ለሚድያችን ተናግረዋል።
ድንገት በተከፈተው ተኩስ ማሰልጠኛ ጣቢያው በእሳት መያያዙን የገለፁት የመሠረት ሚዲያ ምንጮች ተኩሱ እስከ ትናንት ማክሰኞ ጠዋት ድረስ ቀጥሎ ማርፈዱን ተናግረዋል።
ከተኩስ ልወውጡ ጋር በተገናኘ የቆሰሉት ሰልጣኞች በወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ወደ ወልድያ አቅጣጫ ሲጓጓዙ መመልከታቸውን ተናግረዋል።
ለደህንነቷ ሲባል ስሟን እንድንጠብቅላት የጠየቀች አንዲት የወልድያ ከተማ ነዋሪ "ዛሬ ጠዋት የሕክምና ቀጠሮ ስለነበረኝ ወደ ወልድያ ሆስፒታል ሳቀና በመከላከያ ሰራዊት አምቡላንስ ሰባት አስከሬን ተጭኖ ሲወጣ እና ሌሎች ከአስር በላይ የሚሆኑ ቁስለኞች በድንገተኛ የሕክምና ክፍል ውስጥ ሀኪሞች ነብሳቸውን ለማትረፍ ሲሯሯጡ ተመልክቻለሁ" ስትል ተናግራለች።
በወቅቱ ታካሚዎች ከአካባቢው ገለል እንድንል ታዘዝን የምትለው የዓይን እማኟ ጉዳቱ የደረሰው ጃራ ተብሎ በሚጠራው የሚሊሻ ማሰልጠኛ ካምፕ መሆኑን ከሀኪሞቹ መስማቷን ተናግራለች።
ራያ ቆቦ ወረዳ ዞብል 010 ቀበሌ በሚባል አካባቢ ድንገት ታፍሶ የተወሰደ አንድ ወጣት በማሰልጠኛ ጣቢያው ላይ በተፈፀመው ጥቃት ሕይወቱ ማለፉን ዛሬ ቤተሰቦቹ ለመሠረት ሚዲያ ተናገረዋል።
የሟች ወላጆች እንዳሉት ልጃቸው ከሳምንት በፊት ወደ ቆቦ ከተማ ለገበያ እንደወጣ ታፍሶ ጃራ የወታደር ማሰልጠኛ ካምፕ መወሰዱን እና ዛሬ ጠዋት ከወልድያ ሆስፒታል ተደውሎ አስከሬን ውሰዱ እንደተባሉ ለሚዲያችን ገልፀዋል።
ባሳለፍነው ዓመት በሰሜን ወሎ ዞን በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ታዳጊ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ ተማሪዎች፣ ጎልማሶች እና የአዕምሮ ሕሙማን ሳይቀር ለሚሊሻ ስልጠና በሚል በግዳጅ ታፍሰው ጃራ ማሰልጠኛ ጣቢያ መወሰዳቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
-መሠረት ሚድያ-


