ያልተሰላ የችኮላ ዲፕሎማሲ እና የኢትዮጵያ ፈተና
በአሸናፊ ዲዲሞስ ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠናም ሆነ በመላው አፍሪካ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የደህንነት ሚዛን ውስጥ ትልቅ ሚና ያላት ሀገር ናት። ሆኖም እ.ኤ.አ ከ1993 ዓ.ም. ኤርትራ ከተገነጠለች በኋላ የባህር በር ማጣቷ የኢኮኖሚ ጫና፣ የጂ-ኦፖለቲካ እገታ እና የውጭ ፖሊሲ ግፊት ውስጥ እንድትገባ አድርጓታል።
በአሁኑ ጊዜ ከ95% በላይ የሚሆነውን የወጪና ገቢ ንግዷን በጂቡቲ ወደብ ብቻ ላይ መውደቁ ከፍተኛ የትራንዚት ወጪ እና የስትራቴጂ ተጋላጭነት ዳርጓታል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ችግር የባህር በር ፍላጎት ብቻ አይደለም፤ ዋናው ችግሯ ይህን ፍላጎት ለማሳካት የተመረጠው የፖሊሲ እና የዲፕሎማሲ አካሄድ ነው ብየ አስባለሁ። የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን እንደሚሉት በጂኦፖለቲካ ውስጥ የሚወሰኑ ውሳኔዎች በስሜት ወይም በፈጣን የፖለቲካ ትርፍ ሳይሆን በረጅም ጊዜ የኃይል ሚዛን፣ የኢኮኖሚ አቅም እና የቀጠና መረጋጋት ላይ መመስረት አለባቸው።
በቅርብ ዓመታት የታዩ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት እና የውስጥ ደህንነት ውሳኔዎች ግን በተቋማዊ ጥናት እና በሳይንሳዊ ፖሊሲ ትንተና ላይ ከመመስረት ይልቅ በችኮላ እና በግለሰባዊ ውሳኔ ላይ የተመሰረቱ መሆናቸው ብዙ ችግሮችን አስከትሏል።
የሶማሊላንድ የመግባቢያ ሰነድ (MoU) ከዚህ ግልጽ ምሳሌ ነው።
ኢትዮጵያ ፈጣን የባህር በር እና የባህር ኃይል ለማግኘት በማሰብ ከሶማሊላንድ ጋር የፈረመችው ስምምነት በሶማሊያ መንግስት ዘንድ እንደ ሉዓላዊነት ጥሰት ተቆጥሯል። ይህም ሶማሊያን ከግብፅ ጋር ወታደራዊ እና የደህንነት ትብብር እንድታጠናክር አድርጓታል። በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት ስትሞክር አዲስ የቀጣና የደህንነት ስጋት ውስጥ ገብታለች።
ይህ ችግር የተፈጠረው ተቋማዊ አሰራር በመጣሱ ነዉ፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከተቋማዊ መዋቅር (ከዉጭ ጉዳይ መ/ቤት) ውጪ ሲወሰን ምን ያህል አደገኛ እንደሚሆንም ይህ ማሳያ ነዉ። ጠንካራ ሀገራት የሚገነቡት በተቋማት ነው እንጂ በግለሰቦች ፈጣን ውሳኔ አይደለም። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የጥናት ተቋማት እና የስትራቴጂ ባለሙያዎች ወደ ጎን ሲገፉ ፖሊሲው የማይተነበይ፣ የማይረጋጋ እና የማይታመን ይሆናል።
በተመሳሳይ መልኩ የክልል ልዩ ኃይሎችን በችኮላ ትጥቅ የማስፈታት ውሳኔም የፖሊሲ ችኮላ እና የጥናት እጥረት ውጤት መሆኑን አሳይቷል። በተባበሩት ምንግስት ጸጥታ ሰክተር ሪፎርም(Security Sector Reform (SSR 2021) ላይ የተደረጉ ዓለም አቀፍ ጥናቶች የፀጥታ ተቋማትን ያለ ፖለቲካዊ ስምምነት፣ ያለ ህዝባዊ መተማመን እና ያለ ደረጃ በደረጃ ሂደት ማፍረስ ወደ ግጭት ሊመራ እንደሚችል ያሳያሉ።
በኢትዮጵያም ይህ ሂደት በብዙ አካባቢዎች አዲስ ጦርነት እና አለመረጋጋት እንዲፈጠር አድርጓል።
በውስጥ የደህንነት ችግር ውስጥ እያለች ሀገር ወደ ውጭ የኃይል ማስፋፋት ስትጣደፍ የሚፈጠረው አደጋ ቀላል አይደለም፡፡ የውስጥ አቅም ያልተረጋጋ ሀገር ወደ ውጭ በኃይል ለመስፋፋት ስትሞክር በመጨረሻ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የደህንነት ድክመት ውስጥ ይገባል።
ኢትዮጽያ ያለ ዉጪ ጉዳይ አማካሪዎች እና ተቋም መርነት በፖለቲካ መሪዎች መልካም ፈቃድ በወሰደችዉ እርምጃ የአል-ሸባብ እና ተመሳሳይ አሸባሪ ቡድኖች በቀጣናው የተፈጠረውን የፖለቲካ ግጭት እና የብሔረተኝነት ስሜት በመጠቀም አዲስ የደህንነት ስጋት ለመፍጠር እድል አግኝተዋል።
ስለዚህ ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት በችኮላ ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ምላሽ ሳይሆን ረጅም ጊዜ የስትራቴጂ እይታ ነው።
አንዲት ሀገር የተሳካች ሀገር የምትሆነው በተረጋጋ ዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ ትስስር እና በተቋማዊ አቅም ላይ በመመስረት እንጂ በችኮላ የተወሰነ የጂኦ-ፖለቲካ ጨዋታ አይደለም።
ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የጦርነት ጉሰማ እና ‹‹እንኪያ ሰለንታ›› አይደለም፤ የሚያስፈልጋት የተቋማት ጥንካሬ፣ የሳይንሳዊ ፖሊሲ ትንተና፣ በባለሙያ እውቀት የሚመራ ዲፕሎማሲ ነው።
ከኤርትራ ጋር ያለውን የሰላም ስምምነት ማጠናከር ሲገባን የተደረገዉን ‹‹እርቅ›› ተቋማዊ ማድረግ ሲገባን የግለሰቦች መጨባበጥ ብቻ መደረጉ ልታሰብበት ይገባ ነበር.. አሁንም አልረፈደም፣ ከሶማሊያ ጋር በቱርክ ሽምግልና የተጀመረውን ውይይት መቀጠል፣ ከጂቡቲ፣ ከኬንያ እና ከቀጣናው ሀገራት ጋር የኢኮኖሚ ኮሪደሮችን ማስፋፋት እንዲሁም በታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ውስጥ የዲፕሎማሲ ብስለት ማሳየት ለሀገሪቱ ዘላቂ ጥቅም ያመጣሉ።
ኢትዮጵያ ምርጥ ጭንቅላቶች አሏት። ነገር ግን የተሳካ ሀገር የምትሆነው እነዚህን እውቀቶች በክብር፣ በተቋማዊ ስርዓት እና በሳይንሳዊ የፖሊሲ ሂደት ስትጠቀምባቸው ብቻ ነው።
የአፍሪካ ዲፕሎማሲ መቀመጫ የሆነች ሀገር ለዓለም የሚመጥን ተገማችና ተጨባጭ ዲፕሎማሲ መከተል ይጠበቅባታል።
በተቋማት ግንባታ እናተኩር፣ ለተቋማት ክብር እንስጥ፣ ተቋማዊ አሰራር እንከተል።
| መሠረት ሚድያ |



A number of brilliant Ethiopian career diplomats were forced out/ have left on their own accord in recent years because of the following main reasons:
The Ethiopian Foreign Ministry is hollowed from inside - the wishes & desires of the politicians and their personal friendshps with foreign leaders instead of research and analysis guide the country's foreign policy.
The govt's sysytematic attack on the long-standing pillars of the country's diplomacy - multilateralism, collective security, peaceful conflict resolution. Today, it's sad to see that the country's foreign policy is mostly coercive, transactional and guided by shallow tactical objectives.