በዋሽንግተን ዲሲ እና ለንደን ከተሞች በርካታ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የሚያሳትፍ ሰላማዊ ሰልፍ ሊካሄድ መሆኑ ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- 'የአብሮነት ኢትዮጵያ' በሚል ስያሜ ተሰባስበው ላለፉት ጥቂት ወራት በዋናነት በማህበራዊ ሚድያ አማካኝነት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት ሲያደርጉ የቆዩት አካላት በቅርቡ በዋሽንግተን ዲሲ እና በለንደን ከተሞች በርካታ ኢትዮጵያውያንን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን የሚያሳትፍ ሰላማዊ ሰልፍ ሊካሄዱ መሆኑ ታውቋል።
ሰልፉን የሚያስተባብረው የትዕይንተ-ሕዝብ አዘጋጅ ግብረ-ኃይል የቴክኒክ ኮሚቴ ዛሬ ለሚድያችን የላከው መረጃ እንደሚጠቁመው አንድ የበይነ-መረብ ትዕይንተ-ህዝብ እና ሁለት ሰላማዊ ሰልፎችን በዲሲ እና በለንደን ከተማ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ለማካሄድ እቅድ ይዟል።
"በአሁኑ ወቅት አገራችን ኢትዮጵያ በቅርብ ዘመን ታሪኳ አይታው በማታውቀው መጠን እጅግ አሳሳቢ በሆነ የህልውና አደጋ ላይ ነች። ለአለፉት ሰባት ዓመታት በአገራችን በተካሄደው ህዝብ ጨራሽ የእርስ-በርስ ጦርነት ምክኒያት በሚሊዬን የሚገመቱ ዜጐቻችን ማለቃቸው፣ በቢሊዬን የሚገመት ሀብትና ንብረት መውደሙ አልበቃ ብሎ አሁንም እንደገና ወደ ሌላ ከፍተኛና ቀጠናዊ ጦርነት ውስጥ ልንገባ ተቃርበናል" ያለው ኮሚቴው ይህ አፍጥጦ እየመጣ ያለው አደጋ ያለ ተጨባጭ እና ፈጣን የትግል እርምጃ በቀላሉ ሊቀለበስ አይችልም ብሏል።
አክሎም "በህግ ማስከበርና በባህር በር ጥያቄ ሰበብ እየተጐሰመ ያለው ጦርነት ከፈነዳ ሀገራችን መንግስት-የለሽ ወደ ሆነ ሁለንተናዊ ቀውስ መግባቷ፣ የአፍሪካ ቀንድም የቅርብና የሩቅ የውጭ መንግስታት የውክልና ጦርነት አውድማ በመሆን መቋጫ ወደ ሌለው ትርምስ እንደሚገባ ጥርጥር የለውም። ይህንን እውነታ የተገነዘብን ኢትዮዽያዊያን ወደ ተጨባጭ የህዝባዊ እምቢተኛነት ትግል ለመግባትና እየመጣ ያለውን አደጋ ለመቀልበስ የሚያስችል የሀሳብ ዝግጅት ለአለፉት ሶስት ወራት ስናካሂድ ቆይተናል" በማለት አስታውሷል።
አሁን ላይ የሀሳብ ዝግጅቱ ተጠናቆ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባት የሚሰራ አንድ ግብረ-ሃይል መቋቋሙ የተነገረ ሲሆን ግብረ-ሃይሉ ከተለያዩ ተቋማት እና ተዋቂ ግለሰቦች የተውጣጡ 25 የምክር ቤት አባላት እና 7 የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት እንዳሉት ይፋ ሆኗል።
"ሁሉን-አቀፍ በሆነ አግባብም ኢትዮጵያን እንዲመስልና ሰፊ ማህበራዊ መሰረት እንዲኖረው ተደርጐ የተቋቋመ ግብረ-ሃይል ነው" ያለው ኮሚቴው በቀዳሚነት ሊካሄድ የታሰበው የበይነ-መረብ ትዕይንተ-ህዝብ በዩቲዩብ ከ1 ሚሊዬን፣ በሳተላይት ቲሌ ቪዥን ከ10 ሚሊዬን ያላነሰ ህዝብ በቀጥታ ስርጭት እንዲከታተለው ታቅዶ የሚካሄድ ነው።
በቀጣይም በዋሽንግተን ዲሲ እና በለንደን የሚካሄዱት ሰላማዊ ሰልፎችም ኢትዮዽያዊያን ከብዙ ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በብሄር፣ በኃይማኖት እና በፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለም ሳይለያዩ በብዙ ሺዎች በሚቆጠር መጠን በገፍና በጋራ ወጥተው የሚሳተፉባቸው፣ በዓይነታቸውም ልዩ እና ታሪካዊ ሰልፎች እንዲሆኑ ታቅዶ እየተሰራ ነው ተብሏል።
የትዕይንተ-ህዝቦች ዓላማ በኢትዮጵያዊያን መካከል አዲስ የመተማመን፣ ለጋራ ችግር በጋራ የመቆምና በጋራ የመታገል የተናሳሽነት ስሜትና ተስፋ እንዲጠናከር ማድረግ እንዲሁም የውጭ መንግስታትና ዓለም-አቀፍ ተቋሟት የወቅቱን የኢትዮጵያ ሁኔታ በአግባቡ እንዲገነዘቡ ይደረጋል ተብሎ እቅድ መያዙን ሚድያችን ሰምቷል።
በመጪው ማክሰኞ የካቲት 17 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮዽያ አቆጣጠር ከአመሻሹ 12 ሰዓት (በዋሽንግተን ዲሲ 10:00AM) ጀምሮ የግብረ-ሃይሉ ተዎካዮች ትዕይንተ-ህዝቦቹ መቼ እና እንዴት ሊካሄድ እንደታሰበ ለመገናኛ ብዙሃን ዝርዝር ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
-መሠረት ሚድያ-




