(መሠረት ሚድያ)- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአርሲ ዞን ጥቅምት 10 እና 14 ቀን 2019 ዓ/ም በመርቲ ወረዳ አንጋዳ ቀበሌ ልዩ ስሙ ጎራ ሲሊንጎ 14 ምእመናን፣ በሸርካ ወረዳ ጠሬታ ጮሌ ቢርቦ 46 ምእመናን ግፍን በተሞላ ጭካኔ ተገድለው ሕይወታቸው ማለፉን፣ የ20 ምእመናን መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ መቃጠላቸውን፣ ከ20 በላይ የሆኑ ወገኖቻችን ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል።
"በአርሲ ሀገረ ስብከትና በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ንፁሐን ልጆቻችን ላይ የሚፈጸመው እጅግ አሰቃቂና ዘግናኝ ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ተከታታይነት ባለው ሁኔታ፣ ያለማቋረጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱና ከአሁን በፊትም በዞኑ ሥር በሚገኙ ወረዳዎች በርካታ ምእመናን መገደላቸው የሚታወስ ነው" ያለው ሲኖዶሱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በህዝብ ላይ የደረሰውን እጅግ አሳዛኝ ግፍና መከራ ጥልቅ በሆነ የኃዘን ስሜት ተመልክቶ እንዲህ ዓይነቱ አስነዋሪ ድርጊት በየትኛውም እምነት አስተምህሮም ሆነ በሰው ልጅ ሰብዓዊ መብት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል።
አክሎም "የሃይማኖት ነፃነትና በሕይወት የመኖር ሕገ መንግሥታዊ መብትን የጣሰ፣ ከሃይማኖትም ሆነ ከተፈጥሮ ሕገ ሰብእና የወጣ፣ ተከባብሮ የመኖር ሀገራዊ ዕሴቶቻችንን የሚያጠፋ፣ ሊወገዝ የሚገባው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በመሆኑ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በጽኑ ያወግዛል" በማለት መግለጫ አውጥቷል።
የንፁሐኑ ግድያ እንዲቆም ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላትም ይህን ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ተግባር በይፋ በማውገዝና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን በሕይወት የመኖርና በነጻነት የማምለክ መብትን እንዲያስከብሩልን፣ ይህን አስነዋሪ ድርጊት የፈጸሙትን ወንጀለኞችም ለሕግ በማቅረብ የሕግ የበላይነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ እንዲህ ዓይነቱ አረመኔያዊ ተግባር ከእንግዲህ በኋላ እንዳይደገም አስፈላጊውን የሕግ ከለላ በመስጠት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል በማለት ጥሪውን አስተላልፏል።
ሲኖዶሱ በደረሰው ሕልፈተ ሕይወት የተሰማውን ከፍተኛ ኃዘን ገልዖ "ምእመናን ልጆቻችን በያሉበት ተመሳሳይ ጥቃት እንዳይደርስባቸው መንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግላቸው፣ የሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ችግሩ እስከሚፈታ ድረስ እንደመንግሥት አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርጉና አደጋዎችን ማስቀረት የሚያስችል ሥራ እንዲሠሩ እያሳሰብን ለሟች ቤተሰቦችና ለመላው ኢትዮጵያውያን መጽናናትን በመመኘት በግፍ ሕይወታቸውን ላጡት ወገኖቻችን እግዚአብሔር አምላክ ዕረፍተ ነፍስንና ክብረ ሰማዕታትን እንዲያድልልን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትጸልያለች" ብሏል።
በመጨረሻም በዛሬው ዕለት ጥቅምት 16 ቀን 2019 ዓ/ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ አባላት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም ጸሎተ ፍትሐት እንዲፈጸም፣
ነገ ጥቅምት 17 ቀን 2019 ዓ.ም. ከሥርዓተ ቅዳሴ በኋላ በመላው ዓለም በምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገዳማትና አድባራት በሙሉ ጸሎተ ፍትሐት እንዲደረግ፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከሚመለከተው የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣን ጋር ቀጠሮ ተይዞለት ውይይት እንዲያደርግና በቀጣይም ችግሩን በዛላቂነት ለመፍታት ተገቢው ጥረት እንዲደረግ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ወስኗል፡፡
| መሠረት ሚድያ |



ይህ ሐይማኖታዊ ጭፍጨፋ ስምንት አመት ሙሉ
ያለአንዳች ከልካይ በነፃነት የሚፈፀም ጂምላ
ግድያ እንዴት ነው በህዝብ የተመረጠ መንግስት የሚያስተዳድረውን ሕዝብ በሰላም እንዲኖር ያላደረገው
👉 በቀጥታ በአብይ የደህንነት መዋቅር የሚፈፀም
ጭፍጨፋ ነው ሌላ ምንም አይደለም 4.
ይህ የሐይማኖት ጭፍጨፋ እና የዲሞክራቲቭ ቅየራ
እየተፈፀመ ያለው በቀጥታ በአብይ የደህንነት መዋቅር ነው 4.