በውጫሌ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ልጆቻቸውን በዕጣ ለሚሊሺያነት እንዲሰጡ መወሰኑን ተከትሎ በርካቶች አካባቢውን ለቀው እየተሰደዱ መሆኑ ተሰማ
ዕጣ የደረሳቸውና ወደ ውትድርና መግባት ያልፈለጉ በርካታ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውንና ንብረታቸውን ጥለው ከአካባቢው በመሰወር ላይ ናቸው
(መሠረት ሚድያ)- በአማራ ክልል በተቀሰቀሰውና አሁንም በቀጠለው የፀጥታ ቀውስ ሳቢያ በአምባሰል ወረዳ ውጫሌ ከተማ ከፍተኛ የፀጥታ ኃይሎች (ሚሊሻ) ምልመላ ዘመቻ እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል።
ይህ የምልመላ እንቅስቃሴ በክልሉ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱት የፋኖ ታጣቂዎች ጋር እየተደረገ ላለው ግጭት ተጨማሪ ኃይል ለማሰባሰብ ያለመ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህንን አስመልክቶ ለመሠረት ሚዲያ ከስፍራው የደረሱ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ባለፈው መጋቢት 23 ቀን በአምባሰል ወረዳ ውጫሌ ከተማ ትልቅ የሕዝብ ውይይት ተካሂዶ ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ ከክልል እና ከደቡብ ወሎ ዞን የተወጣጡ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች የተገኙ ሲሆን የክልሉ ምክትል መስተዳድር አቶ አብዱ ሁሴንም በቦታው ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።
ምክትል መስተዳድሩ በወቅቱ ባስተላለፉት ጥብቅ መመሪያ አሁን ያለውን የጸጥታ ስጋት ለመመከትና የፋኖ ኃይሎችን ለመቋቋም ከየአካባቢው የጸጥታ አካላት (ሚሊሻዎች) በስፋትና በአስቸኳይ መዋጣትና መመልመል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ይሁን እንጂ ይህንን መመሪያ ተከትሎ በአካባቢው እየተከናወነ ያለው የምልመላ ሂደት በኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ እንግልትና ስጋት እየፈጠረ መሆኑን የአካባቢው ነዋሪዎች በምሬት እየገለጹ ይገኛሉ። እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ የምልመላ ሂደቱ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሳይሆን “በግዴታና በዕጣ” እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህም የተነሳ ዕጣ የደረሳቸውና ወደ ውትድርና መግባት ያልፈለጉ በርካታ ሰዎች ቤተሰቦቻቸውንና ንብረታቸውን ጥለው ከአካባቢው በመሰወር ላይ ናቸው።
የሚገርመውና ማኅበረሰቡን ይበልጥ ያስቆጣው ጉዳይ ዕጣ ደርሷቸው ያመለጡትን ግለሰቦች ለመያዝ መንግሥት እየተጠቀመበት ያለው ስልት ነው። የጸጥታ አካላት ዕጣ ደርሷቸው የጠፉትን ወጣቶችና ጎልማሶች ማግኘት ሲሳናቸው በምትኩ በቤት ውስጥ የቀሩትን አቅመ-ደካማ ወላጆችን፣ ሚስቶችንና ልጆችን እያሰሩ መሆኑ ተጠቁሟል።
ከዚህም አልፎ፣ ግለሰቦቹ የሚተዳደሩባቸውን የንግድ ድርጅቶችና የሥራ ቦታዎች በፖሊስና በጸጥታ ኃይሎች የማሸግ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል።
ይህ ዓይነቱ አስገዳጅ የሰው ኃይል ምልመላ እና በንጹሐን ዜጎች ላይ እየተወሰደ ያለው የጋራ ቅጣት (Collective Punishment) እርምጃ በውጫሌ ከተማና በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ የስነ-ልቦና ቀውስና ማኅበራዊ መስተጋብር መቋረጥ እየፈጠረ መሆኑ ተነግሯል። ነዋሪዎች “የከተማው ባለስልጣናት የሕዝብን ሰላም መጠበቅ ሲገባው እራሱ የፍርሃትና የትርምስ ምንጭ እየሆነ ነው” ሲሉ ድምፃቸውን እያሰሙ ነው።
በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ያለው የፋኖ ኃይሎች እና የመንግሥት ጦር ግጭት እያየለ በመሄዱ መንግሥት የአካባቢውን የሚሊሻ መዋቅር በመጠቀም ተጨማሪ የሰው ኃይል ለማግኘት የሚገደድበት ሁኔታ መፈጠሩን ታዛቢዎች ይናገራሉ።
ሆኖም ግን ይህ ዓይነቱ በኃይልና በማስገደድ የሚደረግ ምልመላ በሕዝብና በመንግሥት መካከል ያለውን እምነት ይበልጥ የሚያሻክርና የአካባቢውን ሰላም ወደባሰ አዘቅት ውስጥ የሚከት መሆኑን ነዋሪዎች ያስገነዝባሉ።
መሠረት ሚዲያም ይህንን የሕዝብ ሰቃይና እሮሮ መረጃዎችን በማጣራት ለሚመለከተው አካል እንዲደርስ ድምፅ መሆኑን ይቀጥላል።
| መሠረት ሚድያ |


