'ዶ/ር ደቦል' በሚል ስም ማህበራዊ ሚድያ ላይ የጤና ባለሙያዎችን ድምፅ በማሰማት የሚታወቀው ዶክተር ታሰረ
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ የጤና ባለሙያዎች በመላው ኢትዮጵያ ሲያሰሙት የነበረውን ድምፅ እና ሲያቀርቡት የነበረውን የመብት እና የጥቅም ጥያቄ ማህበራዊ ሚድያ ላይ በማስተጋባት የሚታወቀው 'ዶ/ር ደቦል' ለእስር መዳረጉ ታውቋል።
'ዶ/ር ደቦል' በሚል ስሙ የሚታወቀው ዶ/ር ዳንኤል ፈንታነህ ትናንት በባህር ዳር ከተማ ውስጥ እንደታሰረ የመረጃ ምንጮች ለመሠረት ሚድያ አረጋግጠዋል።
ከእስሩ በተጨማሪ 'ዶ/ር ደቦል' የሚለው የፌስቡክ ገፅ በመንግስት አካላት እንደተጠለፈ (ሀክ እንደተደረገ) የታወቀ ሲሆን ከዚህ በፊትም የቴሌግራም አካውንቱን ለመጥለፍ ብዙ ሙከራ ሲደረግ እንደነበር የደረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ዶ/ር ዳንኤል ባህር ዳር በሚገኘው ጥበበ ግዮን ሆስፒታል የፅንስና የማህፀን ህክምና (Obstetrics and Gynecology) የመጨረሻ አመት ረዚደንት ሀኪም ሲሆን ከስድስት ወር በሗላ ምርቃት እንዳለው ታውቋል።
የጤና ባለሙያው 'Debol Surgery Bedside' የተባለ መፅሀፍ የፃፈ እንዲሁም 'MAC Ethiopia' የተባለ የህክምና ባለሙያዎች ከሙያቸው ውጪ ሌሎች ተሰጥዎቻቸውን ፈልገው እንዲያገኙ የሚያግዝ ድርጅትን ከመሰረቱ አንዱ ነው።
ዶ/ር ዳንኤል ምሳሌ የሚሆን፣ ላመነበት ወደሗላ የማይል እና በስራው የተመሰገነ እንደሆነ ባልደረቦቹ ለሚድያችን ተናግረዋል። ከእስሩ በሗላ ፍርድ ቤት ቀርቦ ይሁን እንዲሁም የት ቦታ ታስሮ እንደሚገኝ እስካሁን ግልፅ መረጃ አልተገኘው።
መሠረት ሚድያ ከተለያዩ ቦታዎች የሚደርሱት ተከታታይ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የጤና ባለሙያዎች አድማ ሲጀምሩ የተሳተፉ ግለሰቦች ካለፈው አንድ ሳምንት ወዲህ እየታደኑ ለእስር እየተዳረጉ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት ባወጣው መግለጫ የጤና ባለሙያዎች እስር እና እንግልት መኖሩን አረጋግጧል።
"የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በጤና ባለሙያዎች ማህበር ላይ የጣሉትን እገዳ በፍጥነት በማንሳት ከባለሙያዎቹ ጋር ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ውይይት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል" በማለት ተቋሙ አሳስቧል።
አምነስቲ በተጨማሪም እንደ አማራ ክልል ባሉ ቦታዎች በርካታ የጤና ባለሙያዎች እስር እና ማስፈራርያ እየደረሰባቸው ነው ብሏል።
"ወደስራ ተመለሱ ብለውን ስንመለስ እስር እያካሄዱ ነው። በተለይ ነቃ ያለ እንቅስቃሴ ሲያረጉ የነበሩትን እያሳደዱ እያሰሩ ነው" በማለት አንድ የጤና ባለሙያ ተናግሯል።
መረጃን ከመሠረት!



