የአንዳንድ የፖለቲካ እስረኛ ቤተሰቦች ራስን ከማጥፋት እስከ ጎዳና መውጣት እየደረሱ መሆኑ ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- በአማራ ክልል በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ እና ግጭት ምክንያት እጃቸው አለበት በሚል ተጠርጥረው ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙ የፓርላማ አባላት፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የማኅበረሰብ አንቂዎች፣ ምሁራን እና የሲቪክ ማኅበራት ድረጅት መሪዎች በቂሊንጦ እና በቃሊቲ እስር ቤቶች ውስጥ ታስረው እንደሚገኙ ይታወቃል።
የሦስት ልጆች እናት እንደሆነች እና ባለቤቷ በአዲስ አበባ ዳቦ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ ሲሰራ እንደነበር የገለፀችልን አንዲት እናት ከሁለት ዓመት በፊት ባለቤቷ በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰውን የፋኖ ታጣቂ ኃይል የሚያወድስ ዘፈን በእጅ ስልክህ ላይ ከፍተህ ስታዳምጥ ነበር በሚል ተጠርጥሮ ያለምንም ፍትሕ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንደሚገኝ ለመሠረት ሚዲያ ተናግራለች።
"ለአንድ ዓመት ያህል ተመላልሼ የጠየኩት ቢሆንም ከዛሬ ዓመት ወዲህ ግን ማረሚያ ቤት ድረስ ሄጄ ለመጠየቅ በትራንስፖርት ገንዘብ እጥረት ምክንያት መመላለስ አቆምኩ" ብላለች።
ስሟን ለደኅንነቷ ሲባል እንድንሸሽግላት የጠየቀችው ይቺ እናት የልጆቿን የዕለት ጉርስ ለመሸፈን በአንድ የሕንፃ ኮንስትራክሽን ውስጥ በቀን ሰራተኝነት ተቀጥራ እየሰራች እንደምትገኝ እና ልጆቿ በምትሰራበት የሲምንቶ መጋዘን ውስጥ እንደሚውሉ ተናግራለች።
"በዚህ ምክንያት ሦስቱም ልጆቼ ለትምህርት የደረሱ ቢሆኑም ሁለቱ የጀመሩትን ትምህርት ለማቋረጥ ተገደዋል። የቤት ኪራይ መክፈል ስላልቻልኩ ባልተጠናቀቁ ጅምር ሕንፃዎች ስር ሸራ ዘርግቼ ኑሮ ከጀመርኩ አንድ ዓመት ሆኖኛል" ብላ እያሳለፈች ያለችውን ችግር አስረድታለች።
መሠረት ሚዲያ ያነጋገራት ሌላዋ የፖለቲካ እስረኛ ቤተሰብ ወንድሟ ከመታሰሩ በፊት በልብስ ስፌት ሙያ ተሰማርቶ ወላጆቹን በመርዳት ታናሽ እህቱን ደግሞ ኮሌጅ ከፍሎ እያስተማረ እንደ ነበር ትናገራለች።
ባሳለፍነው ዓመት ከሚሰራበት የልብስ ስፊት ቤት በመግባት ሰሞኑን ወደ ጎንደር ሄደህ የተመለስከው ፅንፈኞችን ለመረዳት ነው በሚል ታስሮ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እንደሚገኝ ጠቁማለች።
"በዚህ ምክንያት ድርጅቱም ተዘጋ፣ ቤተሰቦቻችንም ተበተኑ። ታናሽ እህታችን በክፍያ ምክንያት ትምህርቷን አቋርጣ ስራ ፍለጋ ብትወጣም ሊቀናት አልቻለም። ባሳለፍነው ሐምሌ ራሷን አጠፋች" ስትል ነግራናለች።
ማረሚያ ቤት በወር አንድ ጊዜ እየሄደች እንደምትጎበኘው የገለፀችው እህት ሌላ የሁለት የፖለቲካ እስረኛ ቤተሰቦች እራሳቸውን እንዳጠፉ እና ከአስር በላይ የሚሆኑ የፖለቲካ እስረኛ ቤተሰቦች መበተናቸውን፣ አንዳንዶቹ ጎዳና መውጣታቸውን ጠቁማለች።
ከአማራ ክልል የፖለቲካ ቀውስ ጋር በተገናኘ እጃቸው አለበት በሚል በሽብር ተጠርጥረው በቂሊንጦ፣ በቃሊቲ፣ በአባ ሳሙኤል እና በዝዋይ እስር ቤቶች ውስጥ ከሦስት መቶ በላይ የፖለቲካ እስረኞች እንደሚገኙ ይታወቃል።
-መሠረት ሚድያ-



