(መሠረት ሚድያ)- በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ውስጥ በአንድ ክፍል ታስረው የነበሩ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች እና ምሁራን አርብ ጥር 15 ቀን 2019 ዓ.ም ምሽት 11:00 ሰዓት ገደማ በማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ትዕዛዝ ወደተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው እንዲታሰሩ መደረጋቸው ተሰምቷል።
እስረኞቹ በኢሰመኮ አማካይነት የቀረበላቸውን የይቅርታ ቅድመ ሁኔታ የያዘ ሰነድ "አንፈርምም" በማለታቸው ምክንያት የተለያዩ ጫናዎችና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙባቸው እንደሚገኝ ተነግሯል።
በቃሊቲ የነበሩ ከ20 በላይ የህሊና እስረኞች ለእስር ምቹ ወደ ያልሆኑ ቦታዎች በመበታተን እንዲዛወሩ ተደርጓል።
ከእነዚህ እስረኞች መካከል ዶክተር ወንድወሰን አሰፋ በከባድ የህመም ስሜት ላይ እያሉ በምሽት ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የተዛወሩ ሲሆን ከሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ተለይተው የጸጥታና የፖሊስ አባላት ብቻ ወደታሰሩበት "ዞን 6" እንዲገቡ ተደርጓል።
ዶክተር ወንድወሰን ካለባቸው የጤና ችግር፣ ከሁኔታው አስፈሪነትና ብቻቸውን ከመሆናቸው የተነሳ "ወደ ውስጥ አልገባም" በማለታቸው እስከ አሁን ድረስ በዞኑ ደጅ ላይ ተቀምጠው እንደሚገኙ ተረጋግጧል።
በጠባብ ቦታና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዲቆዩ መደረጉ የጤና ሁኔታቸውን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳካበበው ተገልጿል።
ለዚህ አስገዳጅ እርምጃ ምክንያቱን ሲጠይቁ "ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው" የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውና ከኮሚሽነር ተክሉ የተሰጠ መመሪያ እንደሆነ ተጠቅሷል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ሌሎች የህሊና እስረኞችም ለከፍተኛ እንግልት መዳረጋቸው ታውቋል።
አቶ ዮሐንስ ቧያለው፣ ዳዊት በጋሻው እና እሱባለው በለጠ ከባድ ወንጀል የፈጸሙና አስፈሪ እስረኞች ወደሚገኙበት በተለምዶ "ታንከር" ተብሎ ወደሚጠራው ማግለያ ቦታ እንዲገቡ ተደርገዋል።
በተጨማሪም ዶክተር ቴዎድሮስ ኃይለማሪያም እና ረዳት ፕሮፌሰር ሲሳይ አውግቸው ከቃሊቲ ወደ ቂሊንጦ ዞን 4 የተዛወሩ ሲሆን ሚካኤል መላክ እና ሌሎች ሁለት እስረኞች ደግሞ ወደ አባ ሳሙኤል ማረሚያ ቤት ተወስደዋል።
ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ፣ አባይ ዘውዱ እና መንበር አለሙን ጨምሮ የሌሎች እስረኞች የገቡበት ቦታ እስካሁን አልታወቀም።
በእስር ላይ የሚገኙ ዜጎች ሰብዓዊ መብትና ህክምና የማግኘት መብት በህግ የተጠበቀ በመሆኑ የዶክተር ወንድወሰን አሰፋ እና የሌሎች እስረኞች የጤና ሁኔታ በአስቸኳይ በተናጠል አካል እንዲጣራ ጥሪ ቀርቧል።
አግባብ ያላቸው አካላት የእስረኞቹን ህይወትና ደህንነት ለመጠበቅ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ፣ ከቤተሰቦቻቸውና ከህግ ጠበቆቻቸው ጋር እንዲገናኙ፣ እንዲሁም የተደረገበትን የዝውውር ህጋዊ መሰረት ግልጽ እንዲያደርጉ ጥሪ እየቀረበ ይገኛል።
| መሠረት ሚድያ |



ጥር 15 ያላችሁትን አስተካክሉት።