(መሠረት ሚድያ)- በትግራይ ክልል እና አዋሳኝ አካባቢዎች እየተደረገ ያለው ውጊያ ተባብሶ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት በክልሉ የሚገኘው የኢትዮ ቴሌኮም የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መቋረጡ ተረጋግጧል።
የአገልግሎት መቋረጡ የተከሰተው ትናንት ሌሊት ከ4፡21 ጀምሮ እንደሆነ ታውቋል።
ምንጮቻችን እንደገለጹት ከሆነ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ሙሉ በሙሉ ቢቋረጥም ለጊዜው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የስልክ አገልግሎት አሁንም እየሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል። ሆኖም ግን የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት መዘጋቱ በክልሉ ነዋሪዎች፣ በንግዱ ማህበረሰብ እና በቤተሰብ ግንኙነቶች ላይ ከፍተኛ የመረጃ ክፍተትና ጭንቅ ፈጥሮ ይገኛል።
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን እየሰጡ ያሉ አንዳንድ ዜጎች እርምጃው የህዝቡን የመገናኘት መብት የሚገድብና ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሲሉ ኮንነውታል።
"ሰላም የራክበና" በሚል መልእክቶችን በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ እያጋሩ የሚገኙት ነዋሪዎች የአገልግሎቱ መቋረጥ ህዝቡን ከመላው ዓለም እና ከቀረው የኢትዮጵያ ክፍል ጋር ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ የሚያቋርጥ በመሆኑ ከፍተኛ ስጋት አሳድሮባቸዋል።
ይህ የቴሌኮም አገልግሎት መቋረጥ የተከሰተው የትግራይ ኃይሎች በክልሉ የሚገኙ አየር መንገዶችን መቆጣጠራቸውንና በረራዎች መቋረጣቸውን ተከትሎ በተፈጠረው አዲስ የፖለቲካና የወታደራዊ ውጥረት ወቅት ነው።
ቀደም ሲል በነበረው አውዳሚ የሁለት ዓመት ጦርነት ወቅትም በተመሳሳይ መልኩ የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶች ተቋርጠው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁን አዲስ በተቀሰቀሰው ግጭት ምክንያት አገልግሎቱ በድጋሚ መዘጋቱ ክልሉ ወደ ቀደመው የመረጃ መገለል አዙሪት እንዳይመለስ ተሰግቷል።
| መሠረት ሚድያ |



እየተዋጉኮ ነው ሁለቱም ወገን፣