የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከመስከረም ጀምሮ ያለ የኋላ የቫት ክፍያ በአስገዳጅነት ማስከፈል ጀመረ
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ በርካቶች የኤሌክትሪክ ክፍያ ሲሞሉ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ ተቆርጦባቸው በምትኩ የሚሞላላቸው ገንዘብ አነስተኛ መጠን ብቻ እንደሆነ ሲናገሩ በብዛት ይታያል።
"ኮዬ ፈጬ አካባቢ የስሪ ፌዝ ካርድ ለመሙላት 28 ሺህ ብር ይዘን ሄደን ከ15 ሺ ብር በላይ እዳ አለባችሁ ተብሎ ቆጣሪው ላይ 7 ሺህ ብቻ ተሞልቶ ነው የመጣው። ለምን ብለን ስንጠይቅ ቫት አስጀምረን ነው አሉን።”
“ይህንን ከመጀመሪያው ማስተካከል የነበረበት መስሪያ ቤቱ ነው፣ የራሱን ስህተት ህዝቡ ላይ መጫን አይከብድም? ማስተካከያው እሺ ይሁን ለምን በአንድ ጊዜ እንዲሆን ተፈለገ? ህዝቡን ለማማረር?" በማለት በተቋሙ የተሰጠ አስተያየት ተመልከተናል።
"በሚገርም ሁኔታ ካርድ ለመሙላት ሄጄ ለመሙላት ከሰጠሁት 1 ሺህ ብር ላይ 542 ብር በራሳቸው ቆርጠው በቀሪ ገንዘቡ ብቻ ካርድ ሞልተው ሰጡኝ። ፍፁም አንባገነንነት የተሞላበት አገልግሎት፣ ለምን ስትል ይህ አስገዳጅ መሆኑን ነው የነገሩን" በማለት ሌላ የተቋሙ ደንበኛ ለመሠረት ሚድያ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እስካሁን በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ደንበኞቹ በዚህ ዙርያ ግልፅ ማብራርያ ባይሰጥም መሠረት ሚድያ የደረሱት አንዳንድ በተቋሙ ቢሮዎች የተለጠፉ ማስታወቂያዎች ክፍያው 'የውዝፍ ቫት' መሆኑን ይጠቁማሉ።
"ካርድ ስትሞሉ እየተጠየቃችሁት ያለው የኋላ ክፍያ ለመኖርያ ቤት ተጠቃሚ ከመስከረም እስከ ህዳር የሶስት ወር፣ ለንግድ ቤት ተጠቃሚ ከመስከረም እስከ ጥር 2017 ዓ/ም የአምስት ወር ቫት ስለተጨመረ መሆኑን እያሳወቅን ለምን ተቆረጠብኝ በሚል ከሰራተኞች [ጋር] በክርክር የሚባክነው ግዜ እናንተኑ ስለሚጎዳ በትእግስት እምድትስተናገዱ እንጠይቃለን" የሚል ማስታወቂያ በተቋሙ እንደተለጠፈ ተመልክተናል።
በሌላ የተቋሙ መስሪያ ቤትም ትእዛዙ ከመንግስት የመጣ መሆኑም በመግለፅ ክፍያ የጠየቀበትን ማስታወቂያ ተመልክተናል።
ተጠቃሚዎች ግን ክፍያውን ወደኋላ ተመልሶ ማስከፈሉ አግባብ እንዳልሆነ እየተናገሩ ይገኛሉ።
"ዛሬ እዚህ አፋር ክልል ውስጥ የ300 ብር ካርድ ለመሙላት ስሄድ ከ500 ብር በላይ እዳ አለበት፣ ይሄን ካልከፈልሽ መሙላት አትችይም ተባልኩ። ምን አይነት እዳ? የካርዱ ብር ካለቀ እንኳ የማያበድር ቆጣሪ ነው ያለኝ፣ አሁንም 160 ብር እያለው ነው አይቼ የመጣሁት። ታድያ ከየት የመጣ እዳ ነው? ብዬ ልክፈላችሁ ስል የተሰጠኝ ምላሽ ቫት ነው የሚል ሆነ። እዳ የሚለው አላስኬድ ሲል ቫት፣ ይሄ ማታለያ ለአንዳንዱ ሊጠቅም ይችላል። ኑሮ ያማረረን ያነሰ ይመስል ይባስ ብሎ በኤሌትሪክ ክፍያ ህዝብ መማረር አለበት? የሌለው በአቅሙ ሞልቶ እዳይጠቀም እየሆነ ነው። ቫትም ከሆነ ተጠቃሚ በሚሞላበት ጊዜ ከሚሞላው መጠን የሚቆረጠውን የቫት መጠን ወዲያው የምን አይቆረጥም?" በማለት ጥያቄ ያቀረቡት ሌላ የተቃሙ ደንበኛ ናቸው።
"እንዲህ ወዝፎ መክፈል የማይቻልበት ደረጃ ማድረስ ለምን አስፈፈለገ? እኔ መሙላት የፈለኩት 300 ብር፣ ከነእዳ/ቫት ተብዬ ሳልወድ በግድ 800 ብር ነው የከፈልኩት ምክንያቱም አፋር ክልል ውስጥ አለመብራት መኖር በጣም ስለሚከብድ። ቀዝቃዛ አገር ብሆን ኖሮ በእርግጠኝነት ዛሬ ቆጣሪያቹህን መልሼ በሶላር እጠቀም ነበር፣ ይህን የህዝብ ምሬት ሰምታቹህ አሰራራችሁን አደምታስተካክሉ ተሰፋ አለኝ" በማለት አስተያየታቸውን አስፍረዋል።
የኤሌክትሪክ እና የውሃ አገልግሎት በገደብ የተጨማሪ እሴት ታክስ (VAT) እንዲከፈልባቸው የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የዛሬ አመት ገደማ ነበር።
ግንቦት 6፤ 2016 ዓ/ም ለምክር ቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ከታክሱ ነጻ የሚሆኑት የገንዘብ ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ ከሚወሰን በታች የኤሌክትሪክ እና ውሃ ፍጆታ ያላቸው ናቸው ተብሎ ነበር።
አዲሱ አዋጅ ለሁለት አስርት ዓመታት በስራ ላይ ቆየውን የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ እና ከዛ በኋላ እሱን ለማሻሻል ሁለት ጊዜ የወጡትን የማሻሻያ አዋጆች ሙሉ በሙሉ የሚሽር ነው።
“አነስተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ያለበትን ወጪ ለማርገብ ሲባል” የኤሌክትሪክ እና የውሃ አገልግሎት ከታክሱ ነጻ ተደርገው እንደነበር አዋጁ ማብራሪያ ላይ ሰፍሯል።
በስራ ላይ ያለው የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ከ20 ዓመት በፊት በ1994 ከወጣ በኋላ ለሁለት ጊዜያት ያህል ማሻሻያ ተደርጎበታል።
መረጃን ከመሠረት!





