ጥቃቅን እና አነስተኛ ሱቅ ያላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ደባል እንዲፈልጉ ተነገራቸው
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ ከሚወጡ አንዳንድ ደንቦች እና ህጎች መሀል ‘ምን ታስቦ ይሆን?’ የሚያስብሉት ብዙዎቹ ናቸው። ለምሳሌ ስስ ፌስታል ይዞ የተገኘ ከ2 ሺህ ብር እስከ 5 ሺህ ብር መቅጣት እና ቆሻሻ ውሀ የደፋን በመቶ ሺህ ብሮች መቅጣት ይገኙበታል።
መሠረት ሚድያ አሁን የደረሰው መረጃ ደግሞ እንደሚያሳየው በመዲናዋ በጥቃቅን እና አነስተኛ ሱቅ ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ዜጎች ደባል እንዲፈልጉ እየተነገራቸው ነው።
ከየቀበሌው የተውጣጡ ሀላፊዎች በየሱቁ እየዞሩ ከመንግስት የተሰጡ ማንኛቸውም የመንገድ ዳር ተርታ ሱቆች ደባል ሰራተኛ እንዲያስገቡ ተነግሯቸዋል።
"እንደየስራችን አይነት አንድ አንድ ሰው፣ ሁለት ሁለት ሰው ወይም ሶስት ሶስት ሰው እንድናመጣ ትዕዛዝ ሰጥተውናል" ብለው ለሚድያችን የተናገሩት አንድ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 03 ነዋሪ ናቸው።
አክለውም እንደ ቡና ጠጡ፣ ልብስ ስፌት፣ ሸቀጣ ሸቀጥ እና ተመሳሳይ ስራ የሚሰሩ ሱቆች ይህን በአስቸኳይ እንዲተገብሩ ተነግሯቸዋል።
"ማንኛውም የሱቅ ባለቤት ሌላ ሱቁን በጋራ የሚጠቀም ሰው እንዲጨምር ተብሏል። ያውም ለነገ ጠዋት መታወቂያ እና ሁለት ፎቶ በመያዝ ቀበሌ አሻራ እንድንሰጥ ተነግሮናል" በማለት የሚናገሩት ደግሞ የኮተቤ አካባቢ ባለሱቅ ናቸው።
"ምን አይነት ነገር እንደሆነ አልገባንም። ለብዙ አመታት የሰራን ሰዎች አለን። እንዲህ አይነት ነገር ገጥሞን አያውቅም። የወር ገቢያችን በግማሽ ሊቀንስ ወይም ሲሶና አንድ አራተኛ ሊሆን ነው ማለት አይደለም? ምን አይነት ጨዋታ ነው?" በማለት ጥያቄ አቅርበዋል።
ሂደቱን እየመሩ ያሉት ደንብ ማስከበሮች ሳይሆኑ የቀበሌ የቢሮ ሰራተኞች መሆናቸው የታወቀ ሲሆን በየሰፈሩ እየዞሩ አሳስበው እየሄዱ መሆኑ ታውቋል።
ደባል አስገቡ፣ ሱቆች በሁለት ሰው ወይም በሶስት ሰው ስም ሊሆን ይገባል በሚለው በዚህ አዲስ አሰራር ዙርያ እስካሁን ከመንግስት አካል የተሰጠ ማብራርያ የለም።
መረጃን ከመሠረት!



