የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የመከላከያ ትብብርን ጨምሮ የተለያዩ ስምምነቶች መፈረማቸውን አስታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በዛሬው ዕለት በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቴዎስ እና የዩናይትድ ስቴትስ የፖለቲካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አሊሰን ሁከር በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የሁለትዮሽ መዋቅራዊ ውይይት ማዕቀፍ ተፈራርመዋል።
ይህ አዲስ ማዕቀፍ በዋናነት በኢኮኖሚ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በመከላከያና ደህንነት ትብብር እንዲሁም በክልላዊ ሰላምና መረጋጋት ዙሪያ በትኩረት ለመስራት የተነደፈ ነው ተብሏል።
ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ለማስፋፋት፣ የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ የደህንነት ትብብርን ለማጠናከር እና በምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚያስችል ቅንጅትን ለመፍጠር እንደሚረዳ ውጭ ጉዳይ አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ከኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቴዎስ ጋር በዚሁ የሁለትዮሽ ውይይት ጎን ለጎን ተገናኝተው መክረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቶሚ ፒጎት እንደገለጹት ማርኮ ሩቢዮ በምስራቅ አፍሪካ የሚነሱ ግጭቶችን በመፍታትና ውጥረቶችን በማርገብ ረገድ ኢትዮጵያ የምትጫወተውን ጉልህ ሚና አድንቀዋል።
ሚኒስትሮቹ በውይይታቸው ወቅት በኢትዮጵያና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን የደህንነት አጋርነት እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያሉ የንግድ ዕድሎችን ለማሳደግ የተወሰዱ ጠቃሚ እርምጃዎችን በተመለከተ ሰፊ ምክክር ማድረጋቸው ተገልጿል።
| መሠረት ሚድያ |


