የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በመሠረት ሚድያ የምርመራ ዘገባ የተጋለጠውን የአይቲ ፓርክ ህገወጥ ኪራይ እንዲቆም ትእዛዝ አስተላለፈ
(መሠረት ሚድያ)- ሚድያችን የዛሬ ሶስት ወር ገደማ 'አለም ባንክ በዲጂታል ፋውንዴሽን በኩል ለኢትዮጵያ የሰጠው 200 ሚልዮን ዶላር ምን ላይ እየዋለ ነው?' የሚል አንድ የምርመራ ዘገባ መስራቱ ይታወሳል።
በዚህ ብዙዎችን ባነጋገረ ዘገባ ላይ የአለም ባንክ የዛሬ አራት አመት 200 ሚልዮን ዶላር መድቦለት ስራ በጀመረው የዲጂታል ፋውንዴሽን ውስጥ በአማካሪነት ተቀጥረው እየሰሩ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦች በአመት እስከ 120 ሺህ ዶላር እየተከፈላቸው እንዳሉ ጠቅሰን ነበር።
በዚሁ ዘገባችን ላይ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር "Internet Exchange Point" በተባለ ፕሮግራም የኢንተርኔት ፍሰት በሀገር ውስጥ የዳታ ማእከል እንዲያልፍ የሚያደርገው ፕሮጀክት በጀት ተይዞ የነበረ ቢሆንም ስራውን ይዞ የነበረው ተቋም ከቢሮው እንዲለቅ ተደርጎ በሌላ እንዲተካ እንደተደረገ እና ይህም ከገንዘብ ጥቅም ጋር የተያያዘ እንደሆነ መረጃ አቅርበን ነበር።
"አይቲ ፓርክ" ተብሎ በሚጠራው ማእከል ውስጥ በዶላር እየከፈሉ የተከራዩ በርካታ ተቋማት እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ገቢ ግን ወደየት እየገባ እንደሆነም እንደማይታወቅ በዚሁ የምርመራ ዘገባችን ላይ ተጠቅሷል።
አሁን የደረሰን መረጃ እንደሚጠቁመው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ውስጥ የሚገኘውን በተለምዶ MCIT ህንፃ ከዚህ በኋላ ተጨማሪ ኪራይ እንዳያከናውን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ታዟል።
አሰራሩ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ የታቀዱትን እና በመከናወን ላይ ያሉትን ፕሮጀክቶች በማስቆም ለፕሮጀቱ ማስፈፀሚያ የተዘጋጁ ክፍሎችን ባፓርኩ ሜኔጅመንት በኩል ላልታቀደለት አላማ ለግለሰቦች ተከፋፍሎ እየተከራየ መሆኑን የሚገልፅ ደብዳቤ ለመሠረት ሚድያ ደርሷል።
ይህ ግንቦት 1/2017 ዓ/ም በኢኖቬሽን እና ቴልኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ይሹሩን አለማየሁ የተፃፈው ይህ ደብዳቤ "የ MCIT ህንፃ ጉዳይ እልባትና ውሳኔ እስገሚያገኝ ድረስ ተጨማሪ ክፍሎች እንዳይከራዩ በጥብቅ እናሳስባለን" የሚለው ውሳኔ አሳልፏል።
በዚሁ እለት የተፃፈ ሌላኛ የሚኒስቴር ደብዳቤ ደግሞ በMCIT ህንፃ ውስጥ በሀይል የተሰበሩ ክፍሎች እንዳሉ ይገልፃል። ይህም በመሆኑ አስቸኳይ የንብረት ቆጠራ እንዲደረግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዟል።
መረጃን ከመሠረት!





