(መሠረት ሚድያ)- በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ታስረው የቆዩት ዶክተር ወንደሰን አሰፋ ወደ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከተዛወሩ በኋላ ተገቢ ባልሆነ እና ለሰው ልጅ የማይመጥን የማስሪያ ቦታ ውስጥ በመታሰራቸው ለከፍተኛ የህይወት አደጋ መጋለጣቸው ተገለጸ።
እንደ መረጃ ምንጮቻችን ገለጻ ከሆነ ዶክተር ወንደሰን ወደ ቂሊንጦ ከተዛወሩ በኋላ ሳምንታት የተቆጠሩ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በዞን 6 በሚገኝና በቆርቆሮ በተከበበ ጠባብ የቅጣት ክፍል ውስጥ ብቻቸውን ታስረው ይገኛሉ።
የታሰሩበት ክፍል ለመንቀሳቀስ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ አይጦችና ልዩ ልዩ ነፍሳት የበዙበት እንዲሁምከአቅም በላይ የሆነ የሽንት ቤት ሽታ የሚያገኛው እንደሆነ ታውቋል።
"ይህ አስቸጋሪ ሁኔታ በዶ/ር ወንደሰን ጤንነት ላይ ፈጣንና አደገኛ የጎንዮሽ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል። ዶ/ር ወንደሰን የደም ግፊት ህመምተኛ እንደመሆናቸው መጠን መደበኛ መድኃኒት የሚከታተሉ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ባሉበት አስከፊ አካባቢ ምክንያት ደም ግፊታቸው በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመሩ ህይወታቸው በከባድ አደጋ ላይ ወድቋል" አንድ የመረጃ ምንጫችን ጠቁመዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ግለሰቡ ከፍተኛ የአስም ህመም ያለባቸው በመሆኑ ከእስር ቤቱ ጠባብነት፣ ከሚወጣው መጥፎ ሽታ እና አካባቢውን ከሚያጠቃው ከፍተኛ ንፋስ የተነሳ የመተንፈስ ችግራቸው እየባሰበት መጥቷል።
"የችግሩን አሳሳቢነት የጨመረው ደግሞ ቤተሰቦቻቸው እንዳይጠይቋቸውና ሁኔታቸውን እንዳይከታተሉ ጥብቅ ገደብ መጣሉ ነው። ይህ ሁኔታ ለጤናቸው የሚያስፈልገውን ድጋፍና እንክብካቤ ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ሙሉ በሙሉ አደናቅፎታል" የሚሉት ሌላ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጫችን ናቸው።
ዶ/ር ወንደሰን ያሉበት የማረሚያ ቤት ክፍል እንዲስተካከልላቸውና የህክምና እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ለማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ጥያቄ ቢያቀርቡም እስካሁን ምንም አይነት አዎንታዊ መልስ ማግኘት አለመቻላቸው ታውቋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ የሚወስዱትን የደም ግፊትና የአስም መድኃኒቶች ለማቋረጥ እንዲሁም ምግብ ላለመብላት ውሳኔ ላይ መድረሳቸው ተሰምቷል።
ዶ/ር ወንደሰን አሰፋ የወሰዱትን ይህን ውሳኔ ተከትሎ ለዘመድ አዝማድ ባስተላለፉት መልእክት በቀጣይ በህይወታቸውና በጤናቸው ላይ ለሚደርሰው ማንኛውም አይነት ጉዳትና አደጋ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር እና የፍትህ ተቋማት ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስዱ መሆኑን አስታውቀዋል።
ይህንንም ውሳኔ የሀገሪቱ ህዝብ እና የሀገር ውስጥና የአለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተቋማት ይወቁት ብለዋል።
አቶ ክርስቲን ታደለን ጨምሮ በርካታ የፖለቲከኛ እስረኞች የይቅርታ ደብዳቤ ፈርመው መስከረም መባቻ ላይ መፈታታቸው የሚታወቅ ሲሆን ዶ/ር ወንደሰንን ጨምሮ ሌሎች በርካቶች ግን የሰሩት ወንጀል እንደሌለ በመግለፅ ደብዳቤውን አንፈርምም በማለታቸው አሁንም ታስረው እንደሚገኙ ይታወቃል።
| መሠረት ሚድያ |



ይህም ያልፋል።
ኦህዴዳዊው ገዳይ መንግስትን በአለም ፊት
በሕግ እንጠይቀዋለን ገና