(መሠረት ሚድያ)- በኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ውስጥ ሃይማኖትና ፖለቲካን የመደባለቅ፣ የሙስና እና የብልሹ አሰራር ችግሮች በጥልቅ መስፋፋታቸውን መሠረት ሚድያ በትናንትናው ዕለት መዘገቡ ይታወሳል።
ተቋሙ የብልጽግና ፓርቲንና የብልጽግና ወንጌልን ድንበር በማጥፋት እንዲሁም አገልጋዮች የፖለቲካ ደጋፊ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ ይወቀሳል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የካውንስሉ ጠቅላይ ጸሐፊ ፓስተር ጌቱ ለማ ያለ በቂ የአካዳሚክ ብቃት የዶክትሬት ማዕረግ መያዛቸው፣ ለቤተ ክርስቲያን ቦታና አባል ላልሆኑ ግለሰቦች የዲፕሎማቲክ ፓስፖርት ለማስወጣት ደብዳቤ በመጻፍ ገንዘብ መቀበላቸው እንዲሁም የድምጽ ቅጂ እንዲወጣ መደረጉ በርካታ ብርቱ ትችቶችን አስነስቶ ነበር።
አሁን በደረሰን አዲስ መረጃ መሠረት ፓስተር ጌቱ ለማን ወክላ ወደ ካውንስሉ ልካ የነበረችው የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን በጉዳዩ ላይ ጠንካራ ውሳኔ አስተላልፋለች።
የኢትዮጵያ ቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ዋና ጽሕፈት ቤት ዛሬ ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. በቁጥር 2.30/1-3204/2018 ለፓስተር ጌቱ ለማ በጻፈው ይፋዊ ደብዳቤ እንደገለጸው በግለሰቡ የሕይወትና የአገልግሎት ንጽሕና ላይ በበጎና በክፉ የሚነሱ ዘገባዎችን ተከትሎ የቤተ ክርስቲያኗ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከእርሳቸው ጋር ነሐሴ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. ውይይት አድርጎ ነበር።
በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያኗ የቀረቡትን ክሶችና ነቀፌታዎች እውነትነት ለማጣራት መርማሪ ቦርድ የሰየመች ሲሆን በቤተ ክርስቲያኗ መመሪያና መተዳደሪያ ደንብ አንቀጽ 158.2 መሠረት ቦርዱ አጣርቶ ውሳኔ እስከሚያቀርብ ድረስ ፓስተር ጌቱ ከነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ ከማንኛውም የቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ውክልና ታግደው እንዲቆዩ ተወስኗል።
ደብዳቤው በዋና ጸሐፊው በዶክተር ስምኦን ሙላቱ ተፈርሞ የወጣ ሲሆን ይህ ጊዜ በፓስተር ጌቱና ቤተሰባቸው በግል ሕይወታቸውና በእግዚአብሔር ፊት ራሳቸውን የሚመረምሩበትና የንስሐ ጊዜ እንዲሆንላቸው ተመኝቷል።
በተጨማሪም የደብዳቤው ግልባጭ ለቃለ ሕይወት ቤተ ክርስቲያን ፕሬዚዳንት፣ ለሥራ አስፈጻሚ አባላትና ለአካባቢ ቤተ ክርስቲያናት እንዲሁም ለኢትዮጵያ ወንጌላውያን አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዚዳንት እንዲደርስ ተደርጓል።
ይህ እርምጃ ቀደም ሲል በካውንስሉና በጥቅል አሰራሩ ላይ ይነሱ ለነበሩት ከበድ ያሉ የሙስና፣ የፓስፖርት እና የስልጣን አጠቃቀም ክሶች የመጀመሪያው ይፋዊ ህጋዊና አስተዳደራዊ ምላሽ ሆኖ ተመዝግቧል።
| መሠረት ሚድያ |



