ዶ/ር ዳንኤል ፈንታነህ 'ዶ/ር ደቦል' የጤና ባለሙያዎችን በማንቃት፣ በመቀስቀስ፣ በማደራጀት እና የስራ ማቆም አድማ በማድረግ የሚል ክስ ቀረበበት
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ የጤና ባለሙያዎች በመላው ኢትዮጵያ ሲያሰሙት የነበረውን ድምፅ እና ሲያቀርቡት የነበረውን የመብት እና የጥቅም ጥያቄ ማህበራዊ ሚድያ ላይ በማስተጋባት የሚታወቀው 'ዶ/ር ደቦል' ወይም ዶ/ር ዳንኤል ፈንታነህ ከታሰረ በኋላ ትናንት ፍርድ ቤት መቅረቡ ታውቋል።
ባህር ዳር ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት 'የጤና ባለሞያውን በማንቃት፣ በመቀስቀስ፣ በማደራጀት እና የስራ ማቆም አድማ በማድረግ የሰው ህይወት እንዲጠፋ በማድረግ' የሚል ክስ እንደተመሰረተበት መሠረት ሚድያ ሰምቷል።
ለፖሊስ ተጨማሪ 5 የምርመራ ቀን የተሰጠ ሲሆን ዶ/ር ዳንኤል ከነበረበት 13ተኛ ቀበሌ ከሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ወደ ሰባታሚት ማረሚያ ቤት ማረፊያ ይቀየርልኝ፣ ለ16 ሰው በአንድ ጠባብ ክፍል ውስጥ ነው የታሰርኩት በማለት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት መዘዋወሩ ታውቋል።
ከእስሩ በተጨማሪ 'ዶ/ር ደቦል' የሚለው የፌስቡክ ገፅ በመንግስት አካላት እንደተጠለፈ (ሀክ እንደተደረገ) የታወቀ ሲሆን ከዚህ በፊትም የቴሌግራም አካውንቱን ለመጥለፍ ብዙ ሙከራ ሲደረግ እንደነበር የደረሱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ዶ/ር ዳንኤል ባህር ዳር በሚገኘው ጥበበ ግዮን ሆስፒታል የፅንስና የማህፀን ህክምና (Obstetrics and Gynecology) የመጨረሻ አመት ረዚደንት ሀኪም ሲሆን ከስድስት ወር በሗላ ምርቃት እንዳለው ታውቋል።
የጤና ባለሙያው 'Debol Surgery Bedside' የተባለ መፅሀፍ የፃፈ እንዲሁም 'MAC Ethiopia' የተባለ የህክምና ባለሙያዎች ከሙያቸው ውጪ ሌሎች ተሰጥዎቻቸውን ፈልገው እንዲያገኙ የሚያግዝ ድርጅትን ከመሰረቱ አንዱ ነው።
ዶ/ር ዳንኤል ምሳሌ የሚሆን፣ ላመነበት ወደሗላ የማይል እና በስራው የተመሰገነ እንደሆነ ባልደረቦቹ ለሚድያችን ተናግረዋል።
"ዶ/ር ዳንኤል በ 'Dr. Debol' የፌስቡክ ገፁ የጤና ባለሙያውን ድምፅ ከማሰማት ያለፈ ያደረገው አንዳችም ነገር የለም። ንቅናቄው የሚመራው ማንነታቸውን ባላሳወቁ ከፍተኛ የጤና ባለሞያዎች ነው" በማለት ለሚድያችን የተናገሩት አንድ የጤና ባለሙያ ናቸው።
አክለውም "ዶ/ር ዳንኤል በገፁ ለንቅናቄው እና ለጤና ባለሙያው ድምፅ ከመሆን ያለፈ ያጠፋው የሰው ህይወት የለም። በሚገርም ሁኔታ የ 1 ወር እረፍት (month off) ላይ ስለነበር አድማ እንኳን አላደረገም" በማለት መረጃ ሰጥተዋል።
መሠረት ሚድያ ከተለያዩ ቦታዎች የሚደርሱት ተከታታይ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የጤና ባለሙያዎች አድማ ሲጀምሩ የተሳተፉ ግለሰቦች ካለፈው አንድ ሳምንት ወዲህ እየታደኑ ለእስር እየተዳረጉ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ።
መረጃን ከመሠረት!



