በአማራ ክልል በሁለት ዓመት ውስጥ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ተገደው እንደተደፈሩ የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ ጠቆመ
(መሠረት ሚድያ)- ቢቢሲ ዛሬ ይፋ ያደረገው አንድ ዘገባ እንዳሳየው ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም እስከ ግንቦት 2017 ዓ.ም. ባለው ግዜ ውስጥ ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች በአማራ ክልል ከሚደረገው ጦርነት ጋር በተያያዘ ተደፍረዋል፣ በርካቶቹም ለበሽታ ተዳርገዋል።
የዜና ተቋሙ ለወራት ሲያደርገው በነበረው ክትትል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች የመደፈር እና የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን በመረጃ ማግኘቱን ይፋ አድርጓል።
ምንም እንኳ እውነተኛው ግጭት ነክ የወሲባዊ ጥቃት መጠን ሪፖርት ባለመደጉ እና ባለመርመሩ በትክክል ባይታወቅም፤ ቢቢሲ ያሰባሰበው መረጃ ከሐምሌ 2015 እስከ ግንቦት 2017 ዓ.ም. ድረስ 8 ዓመት እስከ 65 ዓመት ዕድሜ ያላቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደደረሰባቸው ያመለክታል።
ገለልተኛ መገናኛ ብዙኃን በክልሉ ያለውን ግጭት ለመዘገብ በተጣለባቸው ክልከላ እና ገደብ ምክንያት ወደ ክልሉ መግባት ባይችሉም የቢቢሲ የናይሮቢ ጋዜጠኞች ቡድን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ተጎጂዎችን እና የጤና ባለሙያዎችን በማነጋገር ቀውሱ በሰብዓዊነት ላይ እያሳረፈ ያለውን ጠባሳ የሚመለከት መረጃ አግኝቷል።
በአማራ ክልል ግጭቱ ሲጀመር አንስቶ ሁለቱም ተፋላሚ ወገኖች ያለ ፍርድ ግድያ፣ ከሕግ ውጪ እስራት፣ አስገድዶ ስወራ፣ የንብረት ውድመት እና ዘረፋ እንዲሁም ሰፊ ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በማድረስ ይከሰሳሉ።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች መንግሥት ተመጣጣኝ ያልሆነ ጥቃት መፈፀሙን የሚያሳይ ማስረጃ እንዳለ አሳውቀዋል።
ድርጅቶቹ ከዚህ በተጨማሪ የአማራ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች በፀጥታ ኃይሎች እና በሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ሆን ተብሎ በሚፈፀሙ ጥቃቶች ኢላማ እንደሆኑ ይናገራሉ።
ቢቢቢ በአማራ ክልል ስለተፈጠረው ቀውስ መረጃ ለማግኘት 4 በመቶ ከሆኑት የክልሉ 43 ጤና ጣቢያዎች እና የሕክምና ምንጮች መረጃዎች መሰብሰቡን ገልጿል። በእነዚህ ተቋማት ከሐምሌ 18/2015 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 2017 ዓ.ም. ድረስ 2,697 ሰዎች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደደረሰባቸው ሪፖርት አድርገዋል። ከእነዚህም ውስጥ 45 በመቶ የሚሆኑት ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ናቸው።
ከተጎጂዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በደረሰባቸው ጥቃት በአባላዘር በሽታ ሲያዙ፤ በርካቶች ደግሞ ለእርግዝና እና ለከባድ የሥነ ልቦና ቀውስ ተዳርገዋል።
ይሁን እንጂ በርካታ የወሲባዊ ጥቃት ተጎጂዎች መገለልን በመፍራት፣ የአባላዘር በሽታ መያዛቸውን ወይም መፀነሳቸውን ላለማወቅ የተፈፀመባቸውን የመደፈር ጥቃት ሪፖርት ማድረግም ሆነ የሕክምና አገልግሎት ማግኘት አይፈልጉም።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ ወሲባዊ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጨመራቸውን ተናግረዋል።
"እያለቀሱ፤ በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ፤ ለማውራት እየከበዳቸው ነው የሚመጡት" ሲሉ አንድ የጤና ባለሙያ የተጎጂዎችን ስሜት ይገልፃሉ። ሆኖም ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ተጎጂዎች የአጥቂዎቻቸውን ማንነት ለመናገር እንደሚያመነቱ እና ፍትሕን ፈልገው እንደማይመጡ ባለሙያዎች አመልክተዋል። ይህም በከፊል በግጭቱ ምክንያት ሕግ እና ሥርዓት በመስተጓጎሉ ነው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች ለሕክምና ወደ ጤና ተቋማት የሚመጡ ተጎጂዎች በእርግዝና ፍርሃት ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል። ሌሎች ደግሞ ጥቃቱ ከደረሰባቸው በኋላ ዘግይተው ወደ ጤና ተቋማት የመምጣት አዝማሚያ ያላቸው ሲሆን፤ ኤችአይቪን ጨምሮ የአባላዘር በበሽታዎች መከላከያ በማይሠሩበት ወቅት ይደርሳሉ።
በተለይም በጎጃም አካባቢዎች ዘግይቶ ወደ ሕክምና ተቋም የመምጣት አዝማሚያ ከፍተኛ ሲሆን፤ አብዛኞቹ ተጎጂዎች አፋጣኝ የእርግዝና መከላከያ (ፖስት ፒል) እንዲሁም የኤችአይቪ ቅደመ መከላከል አይወስዱም ብለዋል።
ሌላ የጤና ባለሙያ ግጭቱ ባሳደረው የትራንስፖርት መስተጓጎል እና መንገድ መዘጋት ምክንያት በርካታ ተጎጂዎች የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት መቸገራቸውን እንደሚገልፁ ተናግረዋል። አንድ ከፍተኛ የጤና ባለሙያ በዚህም የተነሳ የሕብረሰተሰብ ጤና እና የማኅበራዊ ቀውስ ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
ከጤና ተቋማት በተሰበሰበ መረጃ መሠረት ባለሙያው "የኤችአይቪ [ሥርጭት] እንደሚጨምር የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ። የሥነ አእምሮ እና ሥነ ልቦና ጤና ችግሮች እጅግ የከፋ ደረጃ ሊያደርስ ይችላል" በማለት ስጋታቸውን ሲገልፁ፤ ራሳቸውን ያጠፉ ተጎጂዎች መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
በ2015 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር አሃዛዊ መረጃ የአማራ ክልል የኤችአይቪ የሥርጭት ምጣኔ ከ100 ሰዎች 1.1 [ከ1,000 ሰዎች 111 ሰዎች] መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን፤ ይህም ከብሔራዊው አማካኝ ምጣኔ ከፍ ያለ ነው።
የመድፈር ጥቃቶች በግጭቱ እየተሳተፉ ባሉት በሁለቱም ተፋላሚ ኃይሎች እየተፈፀሙ ቢሆንም የጤና ባለሙያዎች ከፋኖ ታጣቂዎች በበለጠ የመንግሥት ወታደሮችን ማየታቸውን ተናግረዋል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ እና ለመረጃ ቅርብ የሆኑ አንድ የመንግሥት ሠራተኛም ከፋኖ ጋር የተያያዙ ጥቃቶች "ውስን" መሆናቸውን የጤና ባለሙያዎችን ሀሳብ በማጠናከር ገልፀዋል።
አብዛኞቹ የአስገድዶ መድፈር ጥቃቶች መከላከያ ሠራዊት ካምፕ በመሠረተባቸው እና በሚቆጣጠራቸው ከተሞች አካባቢ የተፈፀሙ ቢሆንም፤ ባለሙያዎች የከተማ ነዋሪዎች የተሻለ ግንዛቤ እና የጤና አገልግሎት ስለሚያገኙ ጥቃቶችን ሪፖርት የማድረግ አዝማሚያቸው ከፍ ያለ ነው ብለዋል።
ምንጭ: ቢቢሲ




መሐረነ አብ
😥