#አስተያየት ፍትህ ያጣች ነብስ: የቀነኒ አዱኛ ጉዳይ!
(መሠረት ሚድያ)- ቀነኒ አዱኛ እጅግ አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ህይወቷ ካለፈ አስር ወራት አልፏል፣ የእርሷ ሞት እና የተከሰቱት ሁነቶች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን አስከፊ የፍትህ እውነታ አጋልጠዋል። ፆታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ከብሄር ፖለቲካ ጋር ሲጋጩ ፍትህ ለድርድር እንደሚቀርቡ ሞቷ ቁልጭ አርጎ አሳይቷል።
ቀነኒ ወጣት፣ የተማረች እና ተስፋ የነበራት ልጅ ነበረች፣ የህግ ስርአቱ ግን የአንዲት ሴት ህይወት መቀጠፍ ከቁብ የቆጠረው አይመስልም።
የቀነኒን ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ከሚያደርጉት ጉዳዮች አንዱ የወንጀል ተጠያቂነትን በሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ አማራጭ የግጭት መፍቻ መንገዶችን ወይንም ሽምግልናን ለመጠቀም የተደረገው ሙከራ ነው።
አማራጭ የግጭት መፍቻ ስርአት በባህል እና በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ በአንዳንድ ሁኔታዎች ጥቅም ላይ መዋሉ ተገቢ ይሆናል። ይሁንና ግድያን የሚጨምር ጉዳይ ላይ ሽምግልናን ለመጠቀም መሞከር ወንጀል ፈፃሚዎችን ለመጠበቅ፣ ወዳጅ ዘመዶች ላይ ጫና ለመፍጠር እና ተጎጂዎችን ፍቆ ለመሰረዝ የሚደረግ ሙከራ ከመሆን ባለፈ ይህ ነው የሚባል ጥቅም የለውም።
የቀነኒ አሟሟት አጠራጣሪ በሆኑ ሁኔታዎች የተከሰተ ነው። ጉዳዩን ህግ እና ህግ ብቻ ነው ሊፈታው የሚገባ፣ ይህን አሰቃቂ ወንጀል በሽምግልና ለመፍታት መሞከር ከህግም ከሞራልም መቃረን ነው። ከመጀመሪያው ጀምሮ ምርመራውን ለማለዘብ፣ ተጠያቂነትን ለማዘግየት እና ለተጠርጣሪው መውጫ መንገዶችን ለመፍጠር በግለሰቦች እና በተቋማት ጭምር ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል።
ምክንያት? ተጠርጣሪው 'የኛው ነው' በሚለው ብሂል ነው።
በቀነኒ አዱኛ ሞት ተጠርጣሪው ላይ የተነሳው ውዝግብ ከሀገሪቷ ፖለቲካ ጋር የተያያዘ ነው ምክንያቱም ተጠርጣሪው ታወቂ ዘፋኝ ሆኖ ነበር፣ ይህ ደሞ ልጁን በተከለለ የፖለቲካ ስፍራ ውስጥ እንዲቀመጥ አድርጎታል።
የቀነኒ ህልፈተ ህይወት ይፋ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ብዙ ኢትዮጵያውያን የወንጀል ሂደቱ ገለልተኛ በሆነ መንገድ ሊካሄድ አይችልም የሚል ስጋት የገባቸው በዚህ ምክንያት ነበር።
መንግስት ተጠርጣሪውን ነፃ ለማውጣት በሚመስል ሙከራ በዋስ እንዲለቀቅ፣ ጉዳዩ እንዲጓተት እና እንዲረሳ ጥረት ማድረጉን ተመልክተናል። ምናልባትም በጣም አሳዛኝ የሆነው ውድቀት ተቋሞች ያደረጉት ነገር ሳይሆን ለማድረግ ፈቃደኛ ያልሆኑት ነው።
ግልጽ የሆነ የፎረንሲክ ውጤት የለም፣ በልጅቷ አሟሟት ዙሪያ ግልፅ የሆነ መረጃ የለም። የልጅቷን ሞት ለማድበስበስ በሚደረገው ጥረት የቀነኒን ጉዳይ በባህላዊ የኦሮሞ አባገዳዎች ስርዓት በእርቅ ለመቋጨት ጥረት ሲደረግ የሰነበተው ለዚህም ይመስላል።
የሟች ቤተሰቦች ጉዳዩ በሽምግልና መታየቱ አብቅቶ መደበኛ ፍርድ ቤት እንዲይዘው ጠይቀዋል፣ የጠፋው የሰው ህይወት ነውና መንግስት ጉዳዩን ከፖለቲካ በላይ ተመልክቶ ሟች እና ወዳጅ ዘመዶቿ ፍትህ ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ ሊፈልግ ይገባል።
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።




