#አስተያየት እስራኤል ለሶማሊላንድ የሰጠችው የሀገርነት እውቅና እና በኢትዮጵያ ስትራቴጂያዊ አቀማመጥ ላይ ያለው ጥልቅ አንድምታ
የቀድሞ ዲፕሎማት ኢብራሂም ሀሞ ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- እስራኤል እ.ኤ.አ ዲሴምበር 26 2025 ለሶማሊላንድ የሰጠችው ይፋዊ የአገርነት እውቅና በአፍሪካ ቀንድ የጂኦፖለቲካ ኃይል አሰላለፍ ውስጥ በእጅጉን ለውጥ እንደሚያመጣ ይታመናል።
እርምጃው በሁለትዮሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ጥቅም ብቻ የታጠረ ሳይሆን በቀጥታ በባሕር ላይ ደኅንነት፣ በቀጠናዊ ጥምረት እና በቀይ ባሕር - በኤደን ባሕረ ሰላጤ ላይ ባለው የኃይል ሚዛን ላይ ተጽዕኖውን ያሳርፋል።
ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ላላት እና ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ለምታስመዘግበው ወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ፣ ይህ እርምጃ እስትራቴጂካዊ ዕድሎችንም ሆነ ከባድ ስጋቶችን ይዞ መጥቷል።
በመሠረቱ የእስራኤል ውሳኔ የሶማሊላንድን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ከፍ የሚያደርግ ሲሆን ኢትዮጵያን ደግሞ የመካከለኛው ምስራቅ ኃይሎችን፣ ዓለም አቀፍ ተዋናዮችን እና የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ባካተተ ውስብስብ ቀጠናዊ ሽኩቻ ውስጥ ይከታታል።
ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ የተገለለችበት የባህር በር ጉዳይ
ኢትዮጵያ በጎረቤት አገር ወደብ ላይ ጥገኛ መሆኗ ለረጅም ጊዜ ስትራቴጂካዊ ተጋላጭ እንድትሆን አድርጓታል። ከ95 በመቶ በላይ የሚሆነው የአገሪቱ የውጭ ንግድ በጅቡቲ በኩል የሚያልፍ በመሆኑ፣ ይህ ሁኔታ አገሪቱን ለከፍተኛ ወጪ እና ለጂኦ-ፖለቲካዊ ጫናዎች ዳርጓታል።
እስራኤል ለሶማሊላንድ የሃገርነት እውቅና መስጠቷ፣ ሶማሊላንድ እ.ኤ.አ. በ1991 ያወጀችውን ራስ ገዝነት (self-governance) ያጠናክረዋል። ይህም ኢትዮጵያ በ2024 ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ሰነድ ሊያጠናክረው እንደሚችል ይጠበቃል።
የመግባቢያ ሰነዱ በበርበራ አቅራቢያ የሚገኝ የባህር ዳርቻን ለረጅም ጊዜ በኪራይ መውሰድን እና በምላሹም ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የሀገርነት እውቅና የመስጠት እድልንና ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ያካትታል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (DP World) አማካኝነት ከ2017 ጀምሮ የለማው የበርበራ ወደብ፣ ለኢትዮጵያ እንደ ቡና፣ የቀንድ ከብቶች እና ማዕድናት ላሉ የወጪ ንግዶች ምቹ አማራጭና የንግድ መስመር ይከፍታል። በተጨማሪም በጅቡቲ ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ እና የአሰብ ወደብን ብቸኛ አማራጭ አድርጎ የሚታየውን ፖለቲካዊ ውዝግቦች ማስወገድ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስትራቴጂካዊ መፍትሄ ይሆናል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጨምሮ ምዕራባውያን አገሮች የእስራኤልን ፈለግን የሚከተሉ ከሆነ፣ ሶማሊላንድ ተጨማሪ ኢንቨስትመንትን ልትስብ ትችላለች፤ ይህም በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ እና የንግድ መስፋፋት ትልሞችን ያጠናክራል።
ኢትዮጵያ ችላ ልትላቸው የማይገቡ ስጋቶች
ምንም እንኳን ስትራቴጂካዊ ጥቅሞቹ ግልጽ ቢሆኑም፣ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ ስጋት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሁኔታዎች አሉ። እስራኤል ለሶማሊላንድ እውቅና መስጠቷ በሶማሊያ በኩል እንደ ሉዓላዊነት መጣስ ተደርጎ ይወሰዳል።
በምላሹም ሞቃዲሾ የኢትዮጵያን የባህር በር ፍላጎት (ambitions) በጽኑ ከሚቃወሙ እንደ ግብፅ አሁን ደግሞ የእስራኤል በቀጠናው መከሰት በእጅጉን ስጋት ውስጥ የከተታት ቱርክ ጋር ሞቃድሾ ያላትን ግንኙነት አጥብቃለች። በዚህም የአፍሪካ ቀንድ በሁለት የተለያዩ የጂኦ-ፖለቲካ ቡድኖች እየተከፈለ ሲሆን፣ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ፣ ሶማሊላንድ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና እስራኤልን ያቀፈው በዕራባውያንን የሚደግፍ ጥምረት ተፈጥሯል።
የዚህ ጥምረት ትኩረት በቀይ ባህር ላይ ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ የንግድ መስመሮችን ማስፋፋት እና የቀጣናውን የጸጥታ ትብብር ማሻሻል ላይ ሲሆን።
በሌላ በኩል ደግሞ በሶማሊያ የሚመራው ቱርክን እንዲሁም ግብፅን ያካተተ ተቃዋሚ ቡድን ተመስርቷል። ይህ ጥምረት ትኩረቱን ያደረገው የሉዓላዊነት ጥያቄዎችን በማስከበር፣ በባህር ክልሎች ላይ ቁጥጥርን በማረጋገጥ እና የኢትዮጵያን እያደገ የመጣ ተፅዕኖ በመገደብ ላይ ነው።
ጅቡቲ በኢትዮጵያ ላይ የኢኮኖሚ የበላይነቷን ላለማጣት በመስጋት ሶማሊላንድን ሕጋዊ የሚያደርጉ እርምጃዎችን ትቃወማለች። በኢራን የሚደገፉ ቡድኖች እና የቀጣናው ተቀናቃኞች ኢትዮጵያን የምእራባዊያን ጎራ ምድብ ውስጥ (hostile security bloc) የተካተተች አድርገው ሊመለከቷት ይችላሉ፤ ይህም ለአገሪቱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ውስጣዊ ጫናዎችን እና አለመረጋጋትን ሊያመጣ ይችላል።
በአጠቃላይ የእስራኤል የወሰደችው እርምጃ ቀጣናዊ መልኩን እንዲቀይር የሚያደርግ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ ብልጫን ቢሰጥም፣ በጉልህ የሚታየውን የኃል አሰላለፍና ተለዋዋጭ ሁኔታን በጥንቃቄ መምራትን ይጠይቃል።
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።




