ከሶስት ሳምንት በላይ እስር ላይ የቆዩት የሸገር ኤፍኤም ጋዜጠኞች በዋስ ተለቀቁ
(መሠረት ሚድያ)- ላለፉት ሶስት ሳምንታት እስር ላይ የቆዩት የሸገር ኤፍኤም ጋዜጠኞች ትዕግስት ዘሪሁንና ምንታምር ፀጋው የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በወሰነው መሰረት ዛሬ ከእስር ተለቀቁ።
ሸገር ኤፍኤም በጉዳዩ ዙርያ ያወጣው መግለጫ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛው ምድብ ችሎት ጋዜጠኞቹ በዋስ እንዲለቀቁ የስር ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ማፅናቱን አስታውቋል።
"የፌዴራሉ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጋዜጠኞቹ ትዕግስት ዘሪሁንና ምንታምር ፀጋው በ50 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቁ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት በሰጠው ውሳኔ ቅር በመሰኘት ለፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቆ ነበር" ያለው ሚድያው የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው የጠቅላይ ፍ/ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ነገሩን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለዛሬ መስከረም 14 ቀን 2018 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር ብሏል።
"ጋዜጠኞችቹ ትዕግስት ዘሪሁንና ምንታምር ፀጋው በቁጥጥር ስር በዋሉ 21ኛው ቀን በተለዋጩ ቀጠሮ ቀን ፣ የፌዴራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት የስር ፍርድ ቤት በዋስ እንዲለቀቁ የሰጠው ውሳኔ አፅድቆ መዝገቡን ዘግቷል። በውሳኔው መሰረት ዛሬ ከሰዓት ከእስር ተለቀዋል" በማለት መረጃ አጋርቷል።
ሁለቱ የሸገር ኤፍ ኤም ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ ሜክሲኮ ታስረው እንደቆዩ ታውቋል። ጋዜጠኞቹ የታሰሩት በጤና ባለሙያዎች የስራ ማቆም አድማ ዙርያ ከሶስት ሳምንት በሰሩት ዜና ዙርያ መሆኑ ታውቋል።
"ሸገር ኤፍኤም ለበርካታ አመታት እጅግ የበዙ ለመንግስት ግብዐትነት ጭምር ሆነው የሚያገለግሉ መረጃዎች ላይ ሲሰራ የነበረ ሚድያ ነው። ጥፋት እንኳን ተሰርቶ ከሆነ በብሮድካስት ህጉ መጠየቅ እየተቻለ ወደ እስር መሄዱ አሳዝኖኛል" በማለት አንድ ባልደረባቸው ለሚድያችን ተናግሮ ነበር።
-መሠረት ሚድያ-



