የአለማችን ታዋቂ አትሌቶች የሚሳተፉበት አለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር እንድታዘጋጅ ኢትዮጵያ ተመረጠች
(መሠረት ሚድያ)- ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ግዙፍ እና አለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ለማዘጋጀት እድሉን ከአለም አትሌቲክስ (World Athletics) አገኘች።
'Addis Ababa Grand Prix' የተባለው የአንድ ቀን ውድድር ሚያዝያ 10/2018 ዓ.ም በአደይ አበባ ስታዲየም እንደሚካሄድ የታቀደ ሲሆን የሩጫ፣ ዝላይ እና የውርወራ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ በርካታ አትሌቶች ከፍ ያለ ሽልማት በዶላር ይሰጣቸዋል ተብሏል።
የዓለም አትሌቲክስ የውድድር ዋና ዳይሬክተር ፒርስ ኦክላጋን በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ የሁለት ቀን የስራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተከትሎ "ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውደድሮችን ለማዘጋጀት በቂ አቅም እንዳላትና የተለያዩ ውድድሮችን ወደ ኢትዮጵያ እናስመጣለን ማለታቸው " የሚታወስ ነው በማለት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዛሬ አስታውቋል።
ውድድሩን የዓለም አትሌቲክስ ከፍተኛ ባለሙያዎች የሚመሩት መሆኑን ያስታወቀው ፌዴሬሽኑ ለአገራችን የአትሌቲክስ ሙያተኞች ልምድ ለማግኘት የሚያስችልና ከተለያዩ አገሮች የተወጣጡ አትሌቶች የሚሳተፉበት ከመሆኑ ባሻገር በውድድሩ አሸናፊ ለሚሆኑ አትሌቶች ከፍተኛ ሽልማት የሚያገኙበት ይሆናል ብሏል።
ውድድሩ በኢትዮጵያ መካሄዱ ውጭ ሄደው የመወዳደር እድል ላላገኙ አትሌቶች ትልቅ መድረክ እንደሆነ የተጠቀሰ ሲሆን ለኢትዮጵያም ትልቅ ውድድር የማዘጋጀት ልምድ ሆኖ እንደሚያልፍ ተስፋ ተደርጓል።
ውድድሩ በአለም አትሌቲክስ ደረጃ Bronze ወይም 'ሶስተኛ/መዳብ' ደረጃ ተብለው ከተቀመጡት ውስጥ የሚመደብ ሲሆን አሸናፊዎች እንደ ውድድሩ ቢለያይም ከ3 ሺህ ዶላር እስከ 8 ሺህ ዶላር እንደሚያገኙ ሚድያችን ያረገው ዳሰሳ ያሳያል።
-መሠረት ሚድያ-




