ለድሬዳዋ ህዝብ ድምፅ በመሆን የሚታወቀው ወጣት በቃሉ ምስጋናው በጸጥታ ሀይሎች መታሰሩ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ወጣት በቃሉ ምስጋናው በፍትህ እና በአስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ በተለይ ለድሬዳዋ ሕዝብ ድምጽ በመሆን የሚታወቅ ወጣት ነው።
ከዚህ በፊት የድሬዳዋ ምድር ባቡር ሜዳ ለግለሰቦች እንዲሸጥ በከተማው አስተዳደር ሲታሰብ የነበረውን እንቅስቃሴ በማጋለጥ በርካታ ወጣቶችን ያፈራው ሜዳ እንዳይሸጥ አድርጓል፡፡
በዚህ እና በሌሎችም ጉዳዮች በሚያደርገው የማህበራዊ አንቂነቱ ምክኒያት ለ2 ዓመታት ታስሮ ተፈትቶ ነበር።
ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ቀድሞ ያደርገው ከነበረው ማህበራዊ አንቂነቱ ራሱን አግልሎ ተቀምጦ እንደነበረ ለመሠረት ሚዲያ የገለጹት እናቱ ወ/ሮ አበባ ገብረ ህይወት ከእስር ቤት ወከጣ በኋላ እንቅስቃሴው ተገድቦ ቤት ውስጥ መጽሐፍት ሲያነብ ይውል እንደነበረ ተናግረዋል።
"በቃሉ ከማንም ጋር አይገናኝም ነበረ፣ ነገር ግን ማክሰኞ መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም 11 ሰአት አካባቢ የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት ለጥያቄ ትፈለጋለህ በማለት ወስደውት 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ አስረውታል" ያሉት እናቱ ወ/ሮ አበባ ናቸው፡፡
በማግስቱ ረቡዕ የካቲት 2 ቀን ምሳ ሰዓት አካባቢ በፖሊስ ታጅቦ ወደ ቤት አምጥተውት ቤቱ ከተፈተሸ በኋላ ምንም ያገኙት ነገር ባይኖርም መልሰው ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንደወሰዱት ተናግረዋል።
ወጣቱ በዛሬው ዕለት ወደ ድሬደዋ እንደተወሰደ ሚድያችን አረጋግጧል።
"ወንድማችን ኢንጂነር በቃሉ ምስጋናው ተወልዶ ያደገው ድሬዳዋ ነው፣ ይህ ወጣት ከተማውን ወዳድ እና ለህዝብ መብት የሚቆም ማህበረሰብ አንቂ፣ ሙስናን አበክሮ የሚጋፈጥ የሚያጋልጥም ጭምር ነው" ያለው አንድ ወጣቱን በቅርብ የሚያውቅ እና ለመሠረት ሚድያ መረጃ የሰጠ ግለሰብ ነው።
አክሎም "ይህ ወጣት በከተማው ህዝብ ዘንድ ተወዳጅና ተመስጋኝ ነው፣ በበጎ አድራጎት ስራው በተለይ ይታወቃል። ይህን ወጣት ከዚህ ቀደም ከተማዋ ላይ ያለ የምድር ባቡር ሜዳ ለምን ለግለሰብ ይሸጣል፣ የህዝብ ነው፣ ስንት ታዳጊዎችን ያፈራ በማለት በመቃወም እና ዘመቻ በመክፈት ሜዳው ለህዝብ እንዲመለስ አድርጓል። መነሻው ይህ ሆኖ ሌሎች ነገሮችን በመደማመር አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ አስረው አምጥተው ፈርደውበት 2 አመት ታስሮ ተፈትቶ ነበር" በማለት ሁኔታውን አስረድቷል።
"ለምን በዚህ ያህል ወጣት በሀገሩ እንዲማረር እንደሚደረግ አይገባኝም። ፍትህ ለወንድማችን፣ አቅመ ደካማ እናት እና አባት አለው ወላጅ መሰቃየት የለበትም። ድፍን የድሬደዋ ሰው ይመሰክራል ስለበቃል" የሚሉት ደግሞ ሌላ የድሬዳዋ ነዋሪ ናቸው።
"ድሬዳዋ ከተማ ላይ የመናገር ነፃነት እንደሌለ እና በተለይ ሶሻል ሚዲያ ላይ የተፃፈ ሀሳብ ላይ እንኳን ህዝቡ ላይክም ሼርም ኮሜንትም አይፅፍም ያን ካረገ በማግስቱ ቤት ድረስ ነው የሚኬድለት፣ ትታሰራለህ፣ ማስጠንቀቂያ ይሰጥሀል" በማለት ተናግረዋል።
መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚዲያ ባለሙያዎችን ከማሰር እና ማሳደድ ባሻገር በአገር ውስጥ የሚገኙ ነጻ ሚዲያዎች እና ሀሳብ ሰጪዎች ላይ ጫና መፍጠር መቀጠሉን እንደ ሲፒጄ እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ ተቋማት በሚያወጧቸው ሪፖርቶች ጠቁመዋል።
በቅርቡ ዋዜማ ሬድዮ እና አዲስ ስታንዳርድ ሚዲያዎች ፈቃዳቸው የተነጠቀ ሲሆን ሁለት የዶቸ ቨለ እና ሶስት የሮይተርስ ጋዜጠኞች የስራ ፈቃዳቸው ታግዷል፡፡
ከሁለት ወር በኋላ ከሚከናወነው 7ኛው ሀገራዊ መርጫ ጋር በተገናኘ የጋዜጠኞች እና የማህራዊ አንቂዎች እስር ሊቀጥል ይችላል ብዬ አስባለሁ ያሉት በበቃሉ እስር ጉዳይ ጥቆማ የሰጡን ግለሰብ ናቸው።
-መሠረት ሚድያ-







