ሆሳዕና ከተማ ውስጥ በአሰሪዋ አሰቃቂ ድብደባ እና የአካል መጉደል የደረሰባት ወጣት ፍትህ እየጠየቀች ነው
(መሠረት ሚድያ)- የኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀጽ አስራ አራት "ማንኛውም ሰው ሰብዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለው" ይላል።
ይሁንና በተቃራኒው በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች አረመኔያዊ በሆነ መልኩ በግለሰቦች ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ኢ-ሰብዓዊ የአካልና የስነ ልቦና ጉዳቶች ይፈፀማሉ።
ሚድያችን የደረሰው አንድ መረጃ ይህንኑ ያሳያል።
በፎቶው ላይ የምትታየው ወጣት ምርታለም ዳሮታ ትባላለች። ወጣቷ የተወለደችሁ በዳውሮ ዞን በሎማ ቦሳ ወረዳ በሻይቲ ፉላሳ ቀበሌ ሲሆን በ2007 ዓ.ም በስራ ኑሮን ለማሸነፍ ወ/ሮ ሜሮን መንገሻ ወደተባለች ግለሰብ ቤት ሆሳዕና ከተማ ሄደች።
አሁን ከአባቷ ቤት ከወጣች 10 ዓመት ሞልቷታል። ይሁንና ወደ ቤተሰቦቿ ስትመለስ በሚታየው መልኩ ሰውነቷ በስለት ተቆራርጦ እና የግራ እጇ ተቆርጦ ተገኝታለች።
"የግራ እጇ የለም፣ እግሯ በሚዘገንን ሁኔታ ቁስል በቁስል ነው። በአጠቃላይ እንዲህ ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ በወ/ሮ ሜሮን ቤት የአካል ጉዳተኛ ሆና ተመልሳለች" በማለት ጉዳዩን የተከታተሉ እና ለሚድያችን በማህበራዊ ሚዲያ ያጋሩ የአካባቢው ሰዎች ተናግረዋል።
"ህግ ባለበት ሀገር በሰዉ ላይ እንደዚህ ዓይነት ዘግናኝና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መፈፀሙ እጅግ በጣም ያሳዝናል። የሚመለከታችሁ የዞንና የወረዳ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ኃላፊነት ወስዳችሁ ከመርማሪ ፖሊስና ከህግ ተርጓሚ አካላት ጋር በመተባበር ጉዳዩን በቶሎ አጣርታችሁ ለእህታችን ምርታለም ዳሮታ ድምፅ እንድትሆኑላት እንጠይቃለን" ብለዋል።
ሚድያችን የደረሰው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያሳየው ተጎጅዋ አሁን ዳውሮ ዞን ቤተሰቦቿ ጋር ያለች ሲሆን ጉዳዩ ከአራት ቀን በፊት ለፖሊስ ሪፖርት ተደርጓል።
ፖሊስ ተጠርጣሪዋን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ወይም ምርመራ እንደጀመረ ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።
በቀጣይ ቀናት ጉዳዩን ተከታትለን መረጃ እናቀርባለን።
-መሠረት ሚድያ-






