በፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ውስጥ ያሉ አንዳንድ አመራሮች ለወዳጅ ዘመድ እስከ አምስት የመንግስት ቤቶችን በነፃ እያከፋፈሉ ይገኛሉ፣ እንዴት?
(መሠረት ሚድያ)- በአዋጅ ቁጥር 1236/2012 መሰረት የመንግስት መስሪያ ቤት ማለት ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል በመንግስት በጀት የሚተዳደር እና የፌደራል መንግስት ስራዎች የሚከናወንበት ማናቸውም መስሪያ ቤት ነው ይላል።
ይሁንና መሠረት ሚድያ ያደረገው ምርመራ እንደሚያሳየው የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚባለው ተቋም ከፊሉ የመንግስት፣ ከፊሉ የግለሰቦች ድርሻ ያለበት በሚመስል መልኩ እየተመራ ይገኛል።
ሚድያችን ከመስሪያ ቤቱ ተቋማት ሰራተኞች፣ ከኦዲተሮች እንዲሁም ከአንዳንድ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች ለበርካታ ቀናት ሲደርሱት የነበሩትን መረጃዎች ሲመረምር ቆይቷል።
እነዚህ ከማስረጃ ጋር የቀረቡ መረጃዎች የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ውስጥ ከፍተኛ ሙስና ተንሰራፍቶ አይን ያወጣ ሙሰኝነት እንደተንሰራፋ ያሳያሉ።
ሚድያችን የተመለከታቸው ሶስት ዋና የሙስና አይነቶች የመንግስት ሀብት ምዝበራ፣ ወገንተኝነት እና ጉቦ መቀበል/መስጠት ናቸው።
አንድ የተመለከትነው መረጃ እንደሚያሳየው ሌሎች የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ቤት ሲጠይቁ ማስፈራሪያ ሲደርሳቸው በመስሪያ ቤቱ የሚሰራ አንድ የቡድን መሪ ግን በትንሹ ከእሱ በተጨማሪ ለሶስት ልጆቹ ቤት አሰጥቷል።
ከዚህም በተጨማሪ ይህ ሀላፊ ለሚስቱ ዘመዶች እና ገንዘብ ለሚያቀርቡ ነጋዴዎች ሲኤምሲ አካባቢ የሚያስፈልጋቸውን ቤት እየሰጠ ይገኛል።
"የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከኢሚግሬሽን እና ከቀበሌዎች በበለጠ በኢትዮጵያ ውስጥ ሙስና የሚሰራበት መስሪያ ቤት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። በኃይለ ስላሴ ወቅት መሬት የባላባቶች እንደሆነ ሁሉ አሁን ላይ የፌደራል ቤቶች የሀላፊዎች ቤተሰቦች እና ዘመድ አዝማዶች እና ጉቦ የሰጡ ንብረት ሆኗል" የሚሉት አንድ የተቋሙ ሰራተኛ ናቸው።
ሰራተኛው አክለውም "ለልጆች እና ዘመድ አዝማድ ቤት ማስመራት እጅግ የተለመደ ነው። በእውነቱ ከሆነ ይህን ሳይ በሀገሬ ተስፋ እቆርጣለሁ። አዲስ አበባ ላይ የሚካሄደው የቤት ዘረፋ ድሀው የኢትዮጲያ ህዝብ በድህነት ሲቃ እንባውን ሲያፈስ ፈጣሪ አለመመልከቱ ትቶናል እንዴ ያስብላል" ይላሉ።
ሚድያችን ያጣራው አንድ መረጃ እንደሚያሳየው አንድ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቡድን መሪ ለራሱ ቅንጡ የሆነ ቤት ከተረከበ በኋላ ለቤቱ 465 ብር በወር እየከፈለ ይገኛል። ይሁንና ለቤቱ እድሳት በየዓመቱ በትንሹ ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚወጣበት ሰነዶቹ ያሳያሉ።
"በፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚሰሩ በርካታ አመራሮች የቡድን መሪዎችን ጨምሮ ልጆቻቸው 18 አመት ሲሞላቸው ቤት ይሰጣቸዋል። ለምሳሌ እኔ የማውቀው ቡድን መሪ ለአምስት ልጆቹ እና ለሚስቱ ወንድም ቤት አሰጥቷል። የሚገርመው እነዚህ ልጆቹ ስልጣን የሌላቸው ሲሆኑ የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሰራተኛም አይደሉም" የሚሉት አንድ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የኦዲት ሰራተኛ ናቸው።
"እነዚህ ልጆች ቤቱን ከተረከቡ በኋላ ቤቱን ለማደስ በትንሹ አንድ ሚሊዮን ብር ወጭ ይወጣል። ይህ ብቻ አይደለም፣ ሀላፊዎች እና የቡድን መሪዎች ከቤቱ በተጨማሪ ኪራይ የማይከፍሉበት የንግድ ቤት አላቸው" የሚሉት ባለሙያው በፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የሚሰሩ ሰራተኞች ቅርበት እና ሽርክና ያላቸው ቤት እንደሚመደብላቸው እና ስራቸውን ብቻ የሚሰሩ ሰራተኞች ደግሞ ቤት ሲጠይቁ ዛቻ እና ኔትወርክ ያለው የአሸባሪወች ደጋፊ ነው ተብሎ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ እንደሚሰሙ ተናግረዋል።
"አሁን ቤት መጠየቅ ትተን ፅንፈኛ እንዳንባል ዝም ብለን ቢጭኑን አህያ ቢጋልቡን ፈረስ ሆነን እየሰራን እንገኛለን" የሚሉት ስሜ አይጠቀስ ያሉ ሌላ አንድ የተቋሙ ነባር ሰራተኛ ናቸው።
"በእርግጥ ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ረሻድ ካሚል ከመጡ በኋላ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ተቋም ነው። ከዚህ በላይ ማደግ የሚችል ተቋም ቢሆንም ከእሳቸው በታች ያሉ ቡድኖች ግን ይህን ተቋም እየጋጡት ይገኛሉ" በማለት ያስረዳሉ።
እያንዳንዱ የቡድን መሪ ቤት እንደተሰጠው ማስረጃ ያቀረቡት እኚህ ሰራተኛ "ከቤቱ በተጨማሪም የቤት አበል ተብሎ ከ2,500 ብር እስከ 5,000 ብር ይከፈላቸዋል። አንድ የመስሪያ ቤቱ ሰራተኛ ግን የቤት ኪራይ አበሉ 792 ብር ሲሆን ተከራይቶ የሚኖረው ግን 8,000 ብር ነው" ይላሉ።
የተቋሙ ሰራተኞች በአንድነት የሚናገሩት ቤት ይሰጠኝ ብሎ የሚጠይቅ የመባረር እድሉ ከፍ ያለ መሆኑን ነው።
"አንዱ የቡድን መሪ ሶስት ልጆቹን ቤት አሰጥቷቸዋል፣ እሱም የራሱ አለው። የፕሬዝደንት ታየ አፅቀስላሴ ቤት ሲታደስ የራሱንም በእሳቸው ቤት አስመስሎ አሰርቶታል" የሚሉት ሶስተኛው የተቋሙ ምንጫችን ናቸው።
ሚድያችን የደረሰው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያሳየው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከጥቂት ወራት በፊት የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንን የስራ አፈፃፀም ሊገመግሙ በሄዱበት ወቅት ብዙ ጥያቄዎችን ሳያነሱ የቀሩ ሲሆን በወቅቱ 15,000 ብር አበል ተቀብለው መመለሳቸው ታውቋል።
"ሙስና በፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በእግሩ ቆሞ ሄዷል፣ ግን ዋና ስራ አስፈፃሚውን ሳላደንቅ አላልፍም። ጠንካራ ሰው ናቸው፣ ለሰራተኛው በጣም ያስባል። ከእሱ በታች ያሉት ግን ጋጡት፣ መጠጡት" የሚሉት ሰራተኞች ስም እና መረጃ በመጥቀስ ለቤተሰቦቻቸው የሰጧቸውን ቤቶች ዝርዝር ለሚድያችን አጋርተዋል።
የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽንን በዚህ ዙርያ ለማናገር ያረግነው ሙከራ አልተሳካም። ኮርፖሬሽኑ ለሚድያችን ምላሽ ለመስጠትም ሆነ ሚድያ ላይ ያላዋልናቸውን ሰነዶች ተቀብሎ ምርመራ ለማድረግ የሚፈልግ ከሆነ በራችን ክፍት መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን።
-መሠረት ሚድያ-




