እውቅ የፖለቲካ እስረኞች በዛሬው ዕለት ከፍተኛ ጥበቃ ወደሚደረግበት ቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ መደረጋቸው ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በእስር ላይ የሚገኙ ታዋቂ የፖለቲካ እስረኞች እና የምክር ቤት አባላት በከፍተኛ ጥበቃ ወደሚታወቀው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት በዛሬው ዕለት እንዲዛወሩ መደረጉን የመሠረት ሚዲያ ምንጮች አረጋገጡ።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የፌደራል ማረሚያ ቤት አስተዳደር ሰራተኛ ለሚዲያችን እንደገለጹት ከሆነ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው፣ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ዶክተር ወንደሰን አሰፋ እና ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን ጨምሮ በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ወደ ቃሊቲ እንዲዛወሩ ከተደረጉት ውስጥ ይገኙበታል።
"ይህ የእስር ቤት ዝውውር የተደረገው ያለምንም ቅድመ ማስታወቂያ ሲሆን እስረኞቹ በድንገት ተነስተው ወደ እኛ አዲሱ ማረፊያቸው እንዲያመሩ ተደርጓል" ብለው ማረጋገጫውን የሰጡት ደግሞ የቃሊቲ እስር ቤት ባልደረባ ናቸው።
ለዚህ ድንገተኛና ዝውውር እንደ ዋና ምክንያት የቀረበው በቅርቡ የሚካሄደውን አገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሁከትና ብጥብጥ ከተነሳ ለጥንቃቄ በሚል የተሰጠ የጸጥታ ስጋት መረጃ ነው ተብሏል።
የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት እንዲሁም የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር በጋራ ባጠናቀሩት መረጃ መሰረት በምርጫው ወቅት ብጥብጥ ቢነሳ እነዚህ ታዋቂ እስረኞች ትኩረት ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለመንግስት መቅረቡ ታውቋል።
በመሆኑም መንግስት የጸጥታ ስጋቱን ለመቀነስና እስረኞቹን በቅርብ ክትትል ስር ለማዋል ሲል ይህንን ውሳኔ ማስተላለፉ ተመልክቷል።
እነዚህ የፖለቲካ እስረኞች እስካሁን በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ቆይታ የነበራቸው ቢሆንም መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት የጸጥታ ስጋት አለ በሚል ምክንያት እስካሁን ከአምስት ጊዜ በላይ ከተለያዩ ማረሚያ ቤቶችና ዞኖች ሲያዘዋውራቸው መቆየቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ የአሁኑን ዝውውር ከአሁን ቀደሞቹ ለየት የሚያደርገው እስረኞቹን ከከተማ ዳርቻ ካለው የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት በማውጣት ወደ መሐል ከተማ በማስጠጋት በፌደራል ፖሊስ እና በአገር መከላከያ ሰራዊት ጥምር ኃይል ጥብቅ ጥበቃ እንዲደረግባቸው መደረጉ ነው የሚሉት ምንጮቻችን ናቸው።
ከላይ በስም ከተጠቀሱት ግለሰቦች በተጨማሪ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና ባለሙያዎች የዝውውሩ አካል መሆናቸው ታውቋል።
ዶክተር ካሳ ተሻገር፣ ዶክተር ጫኔ ከበደ፣ ዶክተር ሲሳይ አውግቼው፣ ዶክተር ግብረዓብ አለሙ እና ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻውን ጨምሮ ወደ ሃምሳ የሚጠጉ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች በአሁኑ ወቅት በቃሊቲ ከፍተኛ ጥበቃ ማረሚያ ቤት እንደሚገኙ የመሠረት ሚዲያ ምንጮች አረጋግጠዋል።
ዝውውሩን ተከትሎ በእስረኞች ቤተሰቦች ዘንድ ጭንቀት የተፈጠረ ሲሆን እስካሁን ድረስ በማረሚያ ቤቱ በኩል የተሰጠ ይፋዊ መግለጫ የለም።
| መሠረት ሚድያ |


