ከያዝነው መስከረም ወር ጀምሮ ለመንግሥት ሠራተኞች ይፋ የተደረገው የደሞዝ ማሻሻያ እንዳልተራዘመ የገንዘብ ሚኒስቴር ለሚድያችን ተናገረ
(መሠረት ሚድያ)- መንግስት ቋሚ ደሞዝተኞች ለሆኑ የመንግስት ሰራተኞች የዛሬ ወር ገደማ ይፋ ያደረገው የደሞዝ ጭማሪ ባሳለፍነው ዓመት ከተሰሙ ዓበይት ጉዳዮች አንዱ ነበር።
በዚህ ጭማሪ መሰረት በ2018 ዓ.ም የበጀት ዓመት 160 ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረግ የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ እንዲሻሻል መደረጉን መንግስት የዛሬ ወር ገደማ አስታውቆ ነበር።
የዋጋ ግሽበት እየጨመረ በመጣበት ወቅት ደሞዛቸው በተገቢው መጠን ሊጨምር ያልቻለው የመንግስት ሰራተኞች መረጃውን በእፎይታ እንደተቀበሉት የቅርብ ግዜ ትውስታ ነው።
ይሁንና ባለፉት ጥቂት ቀናት ይህ የደሞዝ ጭማሪው ላልተወሰነ ግዜ መራዘሙን የሚገልፁ መረጃዎች ማህበራዊ ሚድያ ላይ በስፋት ሲሰራጩ ታይተዋል።
እነዚህ መረጃዎች ለመራዘሙ ምክንያት አድርገው ያቀረቡት በአንድ በኩል ክልሎች የተሟላ መረጃ መላክ ስላልቻሉ መሆኑን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከሰሞኑ የአለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ ኢትዮጵያ ያለባትን ብድር የመክፈል ጫና በተመለከተ በቅርቡ በጋራ ያወጡትን መግለጫ በመጥቀስ መረጃውን አሰራጭተዋል።
በዚህ ዙርያ መሠረት ሚድያ የገንዘብ ሚኒስትሩን አቶ አህመድ ሽዴን አነጋግሯል።
አቶ አህመድ በመንግስት ይፋ የተደረገው የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ጭማሪ እንዳልተራዘመ ለሚድያችን የተናገሩ ሲሆን ጭማሪው ከያዝነው መስከረም ወር ጀምሮ ታሳቢ ሆኖ እንደሚከፈል ተናግረዋል።
ሚድያችን ያነጋገራቸው እና ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ ሌላ የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ባልደረባ ለደሞዝ ጭማሪው ዝግጅት መጠናቀቁን በመግለፅ ለሁሉም የመንግስት መስሪያ ቤቶች በጭማሪው ዙርያ ሰርኩላር መተላለፉን ተናግረዋል።
"ይህ ተራዝሟል የሚለው መረጃ ከየት እንደመጣ አላውቅም። መረጃው ለህዝብ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ ከመስከረም የሚጀምር የደሞዝ ጭማሪ ለማስፈፀም ስራ ስንሰራ ቆይተናል። በተባለው ግዜም ተፈፃሚ ይሆናል" በማለት ተናግረዋል።
መንግሥት ለደሞዝ የሚያውለው ወጪ ከአጠቃላይ ወጪው አንጻር ያለው ድርሻ ከ30 እስከ 32 በመቶ እንደሚደርስ መረጃዎች ያሳያሉ።
በዚህም አዲስ የደሞዝ ማሻሻያ መሰረት ዝቅተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደሞዝ ከብር 4,760 ወደ ብር 6,ዐዐዐ እንዲያድግ መደረጉ ይታወሳል። በተጨሜሪም ከፍተኛው የመንግሥት ሠራተኛ ደሞዝ ከብር 21,492 ወደ ብር 39,000 እንዲሁም የዲግሪ ተመራቂ መነሻ ደመወዝ ከብር 6,940 ወደ ብር 11,500 መደረጉ በወቅቱ ይፋ ተደርጎ ነበር። ይህም ለደመወዝ የሚወጣውን ጠቅላላ ዓመታዊ የመንግሥት ወጪ 56ዐ ቢሊዮን ብር ያደርሰዋል ተብሏል።
-መሠረት ሚድያ-




Well
Wow