(መሠረት ሚድያ)- በአማራ እና ትግራይ ክልሎች ውስጥ በተፈጸሙ በርካታ የሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) ጥቃቶች ህጻናትን፣ ነፍሰ ጡር እናቶችን እና አንድ የውጭ ሀገር የሰብአዊ እርዳታ ሰራተኛን ጨምሮ ቢያንስ 48 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን እና ከ130 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ተሰምቷል።
የአይን እማኞች፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ሁለት የህክምና ባለሙያዎች ግድያውን ያረጋገጡ ሲሆን ጥቃቱ ዛሬ ከሰአት ላይ መፈፀሙን ነገር ግን እስካሁን የተጣራ መረጃ እንደሌላቸው ለሚድያችን ተናግረዋል።
በመንግስት ወታደራዊ ኃይሎች እና በክልሎቹ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች መካከል ያለው ግጭት በከፍተኛ ሁኔታ በበረታበት በአሁኑ ወቅት የመንግስት ኃይሎች በግጭቱ ውስጥ የበላይነትን ለመጎናጸፍ እየተጠቀሙባቸው ያሉ የድሮን ጥቃቶች ንጹሃንን እና የሲቪል ተቋማትን ኢላማ እያደረጉ ነው በሚል ከባድ አለም አቀፍ ወቀሳ እና ስጋት እያስተናገዱ ይገኛሉ።
የመጀመሪያው ጥቃት የተፈጸመው ከአዲስ አበባ በስተሰሜን ምስራቅ 400 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ እና ከአጎራባቹ ኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ዜጎች በሚገኙበት የውስጥ ተፈናቃዮች (IDP) ካምፕ ላይ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
የዓይን ምስክሮች እንደገለጹት ከሆነ አራት ተከታታይ የድሮን ድብደባዎች አንዱ ከሌላው በመከተል በካምፑ ላይ የተፈጸሙ ሲሆን ጥቃቱ የተከሰተው ህጻናት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት ወደ ቤታቸው በሚመለሱበት አጋጣሚ ነበር።
በአማራ ክልል በተፈጸመው በዚህ ጥቃት በትንሹ 23 ሰዎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከተጎጂዎቹ መካከል በርካታ ህጻናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶች እና በሰብአዊ እርዳታ ስራ ላይ የተሰማራ አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ እንደሚገኙበት ተረጋገጧል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደተናገሩት ጥቃቱ የበርካቶችን አካላት እስከማሳጣት የደረሰ ከፍተኛ ውድመት ያደረሰ ሲሆን የሟቾች ቁጥር አሁንም ሊጨምር እንደሚችል ስጋት አለ።
የግጭቶችን መረጃ የሚያጠናቅቀው አለም አቀፍ ተቋም ACLED በበኩሉ በአማራው ጥቃት ከ16 እስከ 23 የሚደርሱ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረና በርካቶች መቁሰላቸውን ይፋ አድርጓል። በተጨማሪም ከቀናት በፊት በክልሉ በሌላ አካባቢ እህል በመሰብሰብ ላይ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ በተፈጸመ ተመሳሳይ የድሮን ጥቃት በርካቶች ህይወታቸውን ማጣታቸው ተመልክቷል።
በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ራማ ከተማ ማዕከል በተመሳሳይ መልኩ የድሮን ጥቃት ተፈጽሟል። እንደ ነዋሪዎች ገለጻ የመጀመሪያው ጥቃት ምሽት ላይ እህል (ማሽላ) በጫነ የግል ተሽከርካሪ ላይ የተፈጸመ ሲሆን በጥቃቱ የተበተነውን እህል ለመሰብሰብ በማግስቱ ጠዋት በተሰበሰቡ ንጹሃን ዜጎች ላይ ሁለተኛው የድሮን ጥቃት ተሰንዝሯል።
በዚህ ጥቃት ቢያንስ 25 ሰዎች ወዲያውኑ የተገደሉ ሲሆን የአካባቢው የህክምና ምንጮች እና ነዋሪዎች የሟቾች ቁጥር እስከ 40 ሊደርስ እንደሚችል ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሰራዊትም ሆነ አየር ሀይል ለተሰነዘሩበት የጥቃት ክሶች እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ አልሰጠም። በአካባቢው እየተካሄደ ያለው ግጭት እና በወሰን አካባቢ የሚታየው የወታደራዊ እንቅስቃሴ የቀጣናውን ሰላም አደጋ ላይ እንዳይጥለው እና ተጨማሪ የዜጎችን መፈናቀል እንዳያስከትል ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል።
| መሠረት ሚድያ |



ሊመለስልኝ ያልቻለ ነገር ከታጣቂ ጋር በስህተት ሊፈጠር ይችላል ግን ምንም ታጣቂ በለለበት እና ተፈናቃዮች እደሆኑ እየታወቀ ምን ጥቅም ለማግኘት ነው ማሪያምን እስኪ የተለየ እይታ ወይም መረዳት ካላችሁ አስረዱኝ?????
የጁን ያገኛል በቅርቡ!!!