ባለስልጣናት አፍራሽ ይዞታ ካላቸው ንግግሮች እንዲቆጠቡ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች አሳሰቡ
(መሠረት ሚድያ)- አፍራሽ ይዞታ ያላቸው የባለሥልጣናት ንግግሮች ሊገሩ ይገባል በማለት መኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ እናት ፓርቲ እና ዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ዛሬ ባወጡት መግለጫ አሳሰቡ።
ከባለሥልጣናት አንደበት የሚወጡ የማይጠበቁ ቃላት አንድ ጊዜ ሲሆን የአፍ ወለምታ ተብሎ ሊወሰድ ይችላል ያሉት ፓርቲዎቹ በተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተለያዩ ጊዜያት የሚነገሩ ተመሳሳይ ንግግሮች ሥርዓታዊ የአመለካከት አቅጣጫን የሚያመላክቱ መሆናቸው ግን ጥርጥር የለውም ብለዋል።
ፓርቲዎቹ የሰሜኑ ጦርነት በሚካሄድበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሕወሓትና የትግራይ ክልልን አስመልክቶ 'በሕዝብ አገር መሆን እንፈልጋለን ከኢትዮጵያ ተገንጥለን ካሉ እኮ ራሳቸው የቀረጹት ሕገ መንግሥት ላይ የተቀመጠ እኮ አንቀጽ አለ። በዚያ መሠረት መሄድ ነው!' ብለው መናገራቸውን አስታውሰዋል።
አክለውም በተመሳሳይ መልኩ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በቅርቡ ባደረጉት ንግግር “ለመገንጠል ደግሞ ጉልበት አያስፈልግም። አሠራር ሕገ መንግስት አለ። በዚያ ሂዱ” ሲሉ ተደምጠዋል ብለዋል።
"እነዚኽ በይፋ የተነገሩትን ለአብነት ጠቀስን እንጂ ከቅርብ ጊዜያት ወዲኽ ለብልጽግና ሹማምንት ቅርበት የነበራቸው ግለሰቦች እያወጧቸው ያሉና ማስተባበያም ማስተማመኛም ያልተሰጠባቸው ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው የከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ንግግሮች ጆሮን ጭው የሚያደርጉ ናቸው። የኾነው ኾኖ በይፋም ከመጋረጃ ጀርባም የተነገሩና የተባሉ አደገኛ ንግግሮች በስሕተት የተነገሩ እንዳልኾኑ ከድግግሞሹና ከተናገሩት ባልሥልጣናት ደረጃ ማየት የሚቻል ሲኾን ይኽም ሥርዓታዊ አቋም ነው ወይ?! ለማለት ያስገድዳል" በማለት ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ጠቅሰዋል።
አክለውም "አገር የምትገኝበት መጠነ ሰፊ የርስ በርስ ጦርነት አልበቃ ብሎ ባለፈው ያደናቀፈንና ሚሊዮን ዜጎቻችንን ጭዳ ያደረገው የጦርነት እንቅፋት ዳግም ሊመታን ከቋፍ መድረሱን እያየን ነው፤ ከላይ የተጠቀሱ ንግግሮችም የዋዜማው ነጋሪት መኾናቸው አያጠያይቅም" ብለዋል።
አራቱ ፓርቲዎች ባወጡት ባለ ሶስት ነጥብ አቋም በፌዴራል መንግሥቱም ኾነ በሕወሓት በኩል ባሉ ባለሥልጣናት የሚነገሩ ያልታረሙ ንግግሮችን በጽኑ እናወግዛለን፤ እርምት እንዲደረግባቸውም አጥብቀን እንጠይቃለን፤ በፌዴራል መንግሥቱ እና በሕወሓት መካከል ያለው የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ በአፋጣኝ እንዲቆም እንጠይቃለን እንዲሁም በትግራይ ክልል ከሰሞኑ የተጀመረው መጠነ ሰፊ አፈሳና አስተዳደራዊ ውጥረት በአፋጣኝ እንዲቆም እንጠይቃለን ብለዋል።
መረጃን ከመሠረት!





