አቶ ጌታቸው ረዳ- ከጦር አዝማችነት እስከ ፖለቲካዊ መገለል
(መሠረት ሚድያ)- ለሁለት ዓመት በቆየው የትግራይ ጦርነት ወቅት በሀገር ውስጥ እና በአለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን እየቀረቡ የክልሉን ሁኔታ ሲያስረዱ የቆዩት፣ በሁዋላም የክልሉ ጌዚያዊ አስተዳዳሪ ተደርገው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተሹመው የነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ አሁን እንደ አሮጌ ቁና ተጥለዋል። ሲመሩት ከቆዩት ፓርቲም ገለል እንዲሉ ተደርገዋል።
የአቶ ጌታቸው መገለል በህወሃት ውስጥ ስላለው ጥልቅ ክፍፍል፣ ፖለቲካዊ አሻጥር እና የስልጣን ፍትጊያ የሚያሳይ ነው። ይህ ደሞ ከጦርነት በሁዋላ ወደ ማገገም መስመር የገባው የትግራይ ክልል ላይ መጥፎ ጥላውን አጥልቷል።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ከአላባማ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁት የህግ ምሁር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በትግራይ ጦርነት ወቅት የሕወሃት ቃል አቀባይነት ሚና ከመጀመራቸው በፊት የኢትዮጵያ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር ነበሩ።
ደም አፋሳሽ ግጭቱን ያስቀረው የፕርቶሪያ ስምምነት እ.ኤ.አ መጋቢት 2023 ከተፈረመ በሁዋላ አቶ ጌታቸው የትግራይ ጊዜያዊ ክልላዊ አስተዳደር እንዲመሩ ተሹመው ነበር። ሹመታቸው በግጭት ለደቀቀችው የትግራይ ክልል የለውጥ፣ እርቀሰላም እና አዲስ ምእራፍ ምልክት ተደርጎ ተወስዶ ነበር። ተስፋው ግን ዘላቂ ሊሆን አልቻለም።
ምንም እንኳን አቶ ጌታቸው ክልሉን ለማረጋጋት እና ተጠያቂነትን ለማስፈን ጥረት ያደረጉ ቢሆኑም በራሳቸው የፓርቲ አባላት ከመገፋት አላዳናቸውም።
የተለያዩ ምንጮች እንዲሁም በተለያዪ ጊዜያት ራሳቸው አቶ ጌታቸው እንደገለፁት ከሆነ በዶ/ር ደብረፂዮን የሚመራው ቡድን ከስልጣን እንዲወገዱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጏል። በአቶ ጌታቸው እና በዶ/ር ደብረፂዮን ቡድን መካከል ያለው ግጭት ተባብሶ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሰው ፓርቲው ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ ጌታቸውን ረዳን ጨምሮ 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ባልተገኙበት 14ኛውን ድርጅታዊ ጉባኤ ባካሄደበት ጊዜ ነው።
እ.ኤ.አ መስከረም 2024 ህወሃት አቶ ጌታቸው ረዳን ጨምሮ ሌሎች 15 ከፍተኛ ባለስልጣናትን ከፓርቲው አባረረ። ፓርቲው ለመባረራቸው ምክንያቱ አስተዳደራዊ ችግሮች ናቸው ይበል እንጂ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ሰዎች በፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን የስልጣን ግብግብ እንደምክንያት ያቀርባሉ።
አቶ ጌታቸው ረዳ ራሳቸው ተቀናቃኛቸውን በፓለቲካዊ አሻጥር ከመክሰሰሳቸው ባሻገር የፓርቲው አክራሪ አባላት እንዲታሰሩ ይፈልጉ እንደነበር ይገልፃሉ። ሞታቸውንም የሚሹ ሃይሎች እንዳሉ ይነገራል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳሪነት መነሳታቸው ስለ ክፍፍሉ እንዲሁም በክልሉ እና በፓርቲው ውስጥ ስላለው ችግር አፍረጥርጠው እንዲናገሩ እድሉን ሰጥቷቸዋል።
በፋና ቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ በህወሃት ውስጥ ተሸሸገው ያሉ አመራሮች "የወንጀል ድርጅት" እየመሩ ይገኛሉ ሲሉ ወቀሳቸውን አቅርበዋል። በፓርቲው ውስጥ ስላለው ሙስና እና ዘረፋ፣ ህገወጥ የወርቅ ማእድን ስራ እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታ ምዝበራ በዝርዝር ተናግረዋል።
በህወሃት ውስጥ ያሉ አመራሮች ከኤርትራ ባለስልጣናት ጋር በመተባበር ክልሉን ወደ ዳግም ግጭት የመክተት ፍላጎት እንዳላቸው ፣ ይህም ፍላጎታቸው በተዘፈቁበት ዘረፋ እና ወንጀል ተጠያቂነት እንዳይመጣባቸው ከመፈለግ እንደሆነ አብራርተዋል። እነዚህ የፓርቲው አባላት በጦርነቱ ወቅት የወሰኗቸው ውሳኔዎች በክልሉ አስገድዶ መድፈር ፣ መፈናቀል እና የ"ጅምላ ጭፍጨፋ" ሲሉ የገለፁት አሰቃቂ ድርጊቶች እንዲፈፀም አስተዋፅኦ አድርገዋል ሲሉ ወቅሰዋል።
የክልሉ አለመረጋጋት ቀጥሎ በሁዋላ ላይ የፌደራሉ መንግስት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገባ ተገዷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ እ.ኤ.አ 2025 አቶ ጌታቸው ረዳን ከሃላፊነት በማንሳት በምትካቸው ጄነራል ታደሰ ወረደን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ አድርገው ሾመዋል።
ምንም እንኳን አቶ ጌታቸው ረዳ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ተደርገው የተሾሙ ቢሆንም ብዙ ታዛቢዎች አቶ ጌታቸው የፖለቲካ ግዞት(political exile) ነው የደረስባቸው ይላሉ።
አሁን አቶ ጌታቸው ረዳ ሲያገለግሉት የቆዩት ፓርቲን ዋነኛ ተቺ ሆነው መጥተዋል ፤ በፓርቲው ውስጥም ካለማን አለብኝነት ወንጀል እየተፈፀመ ይገኛል ፤ የተቃውሞ ድምፆችም እየታፈኑ ነው ሲሉ ስጋታቸውን እየገለፁ ይገኛል።
በአቶ ጌታቸው ረዳ ላይ የደረሰው ትግራይ ከጦርነቱ በኋላ የገጠማትን ሰፊ ፈተናዎች ማለትም በክልሉ ለውጥ በማምጣት እና ስልጣንን በማስጠበቅ መካከል፣በሰላም ግንባታ እና ጦረኝነት(militarism ) መካከል በግልፅኝነት እና ስር በሰደደ የፖለቲካ ቁጥጥር መካከል ያለውን ፈተናዎች በከፊል የሚያሳይ ነው።
የአቶ ጌታቸው ረዳ ደጋፊዎች የሪፎርም አጀንዳ በማቀንቀኑ ለውጥ ከማይፈልገው የቆየ ሃይል ጋር የተጋጨ ነው ይላሉ። ተቺዎቹ የስልጣን ግብግቡን ለማሸነፍ ያልቻለ ስልጣን ፈላጊ ነው ሲሉ ይተቻሉ።
ይሁንና በየትኛውም ጎን ቢቆም የአቶ ጌታቸው ረዳ ከስልጣን መወገድ እና የህወሃት ተቺ ሆኖ መውጣት በህወሃት ውስጥ ያለውን ስር የሰደደ የውስጥ ተቃርኖ በግልፅ እንዲታይ ያደረገ እንዲሁም የወደፊቱ የትግራይ የፓለቲካ አካሄድ ላይ ጥያቄ እንዲኖር ያደረገ እንደሆነ ያሳያል።
"ይህን ሁሉ አመታት የታገልኩት ጥቂት ሰዎች ትግሉን ጠልፈው የስልጣን እና የትርፍ መጠቀሚያ አድርገው ለማየት አይደለም” ሲሉ አቶ ጌታቸው በአንድ ወቅት ተናግረዋል። አሁን ወደ እንዲገለሉ የተደረጉት አቶ ጌታቸው ረዳ ውስብስብ ሰው ናቸው።
ለውጥ አራማጅ ፣ የውስጥ ሚስጢር ነጋሪ ወይንስ በውስጥ የፖለቲካ ጦርነት ሰለባ የሆኑ ግለሰብ? ጊዜ የሚፈታው ጥያቄ ነው ።
መረጃን ከመሠረት!



