ዘንድሮ በሚካሄደው በ‘ግራንድ አፍሪካን ረን’ የመዝናኛ ሩጫ ላይ ለአንድ ዕድለኛ ተሳታፊ ዘመናዊ የቶዮታ መኪና በዕጣ እንደሚቀርብ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የዳያስፖራ አባላትን የሚያሰባስበው የ ‘ግራንድ አፍሪካን ረን’ የ5 ኪሎ ሜትር የመዝናኛ ሩጫ ዘንድሮ ለ8ኛ ጊዜ በመጪው ኦክቶበር በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
እ.አ.አ ኦክቶበር 10 ቀን 2026 በሚደረገው ዝግጅት ላይ ከሚሳተፉ ተሳታፊዎች መካከል አንድ ዕድለኛ ተሳታፊ የ2026 የቶዮታ ኮሮላ መኪና በዕጣ እንደሚያሸንፍ ተገልጿል። ዕጣው በዝግጅቱ መጨረሻ የሚወጣ ሲሆን፣ ሽልማቱ በዝግጅቱ ዋና አጋር በሆነው አሌክሳንድሪያ ቶዮታ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል።
በዝግጅቱ ላይ የታዋቂ አትሌቶችና የኪነጥበብ ባለሞያዎች በክብር እንግዳነት እንደሚሳተፉ አዘጋጁ ኖቫ ኮኔክሽንስ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።
የአሌክሳንድሪያ ቶዮታ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ማን አለብህ በሰጡት አስተያየት ግራንድ አፍሪካን ረን ከሩጫ በላይ ለዳያስፖራው ማህበረሰብ የመገናኛ መድረክ እና ለበጎ አድራጎት ድርጅቶች የገንዘብ ማሰባሰቢያ መሆኑን ገልጸው፣ ድርጅታቸው የረጅም ጊዜ ደንበኞቹን ለማመስገን ይህን ሽልማት እንደሚያቀርብ አስረድተዋል።
በተጨማሪም ከዳያስፖራው ጋር ያላቸውን አጋርነት ወደፊትም እንደሚቀጥሉ አስገንዝበዋል።
የግራንድ አፍሪካን ረን ዋና አዘጋጅ ዶ/ር ጋሻው አብዛ በበኩላቸው ዝግጅቱ ከአንድ ቀን የቤተሰብ ሩጫ በላይ ትልቅ ጥቅም እንዳለው ጠቅሰው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያን እንዲሁም ሌሎች አፍሪካውያንን ለማቀራረብ ጉልህ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል።
አዘጋጆቹ እንደገለጹት፣ የመኪናው ሽልማት ለአንድ ዕድለኛ ብቻ ቢሆንም የዕጣ ሂደቱ በዝግጅቱ ቀን አዝናኝና አጓጊ እንዲሆን ዝግጅት ተደርጓል። ዘንድሮ የሚቀርበው የቶዮታ መኪና ለ4ኛ ጊዜ እንደ ሽልማት የሚሰጥ መሆኑም ተጠቅሷል።
የዝግጅቱ ምዝገባ ከሰኔ ወር መጀመሪያ ጀምሮ በድረ-ገፁ www.africanrun.com ላይ እንደሚጀመር አዘጋጆቹ ጨምረው አስታውቀዋል።
-መሠረት ሚድያ-



