በግል ፀብ መሀል የቪአይፒ እጀባ የፀጥታ አባላትን በስልክ በመጥራት ህዝብን ያሳዘነው የጋዜጠኛው አነጋጋሪ ድርጊት
(መሠረት ሚድያ)- በሀገራችን አልፎ አልፎ አንዳንድ ባለስልጣናት እንዲሁም ለባለስልጣናቱ ቅርብ የሆኑ ግለሰቦች ህዝብን የሚያሳዝኑ እና የሚያነጋግሩ ድርጊት ሲፈፅሙ ይታያል።
ዛሬ የምናስነብባችሁ ግለሰብ የዚህ አንድ ማሳያ ነው።
ለቻይናው 'CGTN' ሚድያ ሲሰራ የሚታወቀው ጋዜጠኛ ግሩም ጫላ ከተማ ውስጥ በሚፈፅማቸው አንዳንድ ድርጊቶች አነጋጋሪ መሆኑ አዲስ ባይሆንም በትናንትናው እለት የፈፀመው ግን ብዙዎችን አሳዝኗል፣ አስቆጥቷልም።
ድርጊቱ የተፈፀመው ትላንት እሁድ ነሃሴ 25 ከቀኑ ወደ 11 ሰአት ገደማ ነው።
ጋዜጠኛው ካዛንችስ/እንደራሴ አካባቢ ይገኛል ወደተባለ ቤቱ እየነዳ እየገባ ሳለ የተለመደ የመንገድ ላይ ፀብ በእርሱ እና በሌላ የራይድ አሽከርካሪ መሀል መፈጠሩን ጉዳዩን የተከታተሉ ምንጮች ይናገራሉ።
"ቦታውን አልፎ ወደ ቤቱ ገባ፣ ትንሽ ቆየት ብሎ ግን እጅግ የአካባቢውን ሰው ያስደነቀ እና ለማመን የቸገረ ነገር ተፈጠረ። ለወትሮው ቪአይፒ እንግዳ ሲመጣ ለፀጥታ ስራ ቦሌ መንገድ ላይ የምንመለከታቸው 3 ነጫጭ የፌደራል ፖሊስ V8 ተሽከርካሪዎች ሳይረን እያሰሙ በርካታ ፖሊስ ጭነው መጡ" በማለት ድርጊቱን በስፍራው ሆነው የተከታተሉ አንድ ግለሰብ ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
አክለውም "ቀደም ሲል የተጣለው የራይድ ሹፌር ተሽከርካሪውን እየነዳ ከስፍራው የሄደ ቢሆንም ጋዜጠኛው ከቤቱ ተመልሶ ወጥቶ በማን አለብኝነት በመኪናው መንገድ ዘግቶ እና ወርዶ ሲንጎማለል ስንመለከተው ነበር" በማለት የታዘቡትን ተናግረዋል።
ሚድያችን በተጨማሪ ከሌሎች ምንጮቹ እንዳረጋገጠው የፌደራል ፖሊስ አባላቱ እንደራሴ ሰፈር የሚገኘው ሰፋ ስጋ ቤትን በመውረር 'ልጁን አምጡ!' በማለት በወቅቱ እዛ የነበሩት ተጠቃሚዎችን ጭምር ሲያስጨንቁ ማምሸታቸው ታውቋል።
"በቦታው እስከ ምሽቱ 4 ሰአት ነበሩ። የተፈጠረውን ግርግር በስልክ ለማስቀረት አስቤ ነበር ቢሆንም የፀጥታ ሰዎቹ ሁኔታ ግን እጅግ ያስፈራ ነበር። ለአንድ ግለሰብ ለዛውም ለማይረባ የመንገድ ላይ የሹፌሮች ስድድብ በዚህ ደረጃ ህዝብ ሲጨነቅ ማምሸቱ ትንግርት ነው" በማለት አንድ የአይን ምስክር ተናገረዋል።
"የዜጎች ደንነት በዚህ መጠን በግለሰቦች መሻት አደጋ የሚፈጠርበት ሁኔታ ማየቴ አስፈራኝ። ወደ ነበርንበት ጊዜ መመለሳችን ስመለከት በጣም አዘንኩ። እውነት ለመናገር ለመጀመሪያ ጊዜ ካገሬ መሰደድ አማረኝ" በማለት ስሜ ይቅር በሚል ምንጩ ተናግሯል።
ግለሰቡ እዚሁ እንደራሴ አካባቢ ከዚህ በፊትም አንዳንድ በቀን ስራ፣ በሊስትሮ፣ መኪና በማጠብ የሚተዳደሩ ዜጎችን እንዲሁም በአካባቢው ባሉ ተማሪዎች ላይ ማስፈራራት ሲያደርስ እንደነበር ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
ጋዜጠኛ ግሩም ከዚህ ቀደም ግሎባል ቴሌቭዥን ኔትዎርክ ኦፍ አፍሪካ (GTNA) በሚል ስያሜ የተቋቋመው እና በአፍሪካ ግዙፉ የሚድያ ተቋም ይሆናል የተባለለት ድርጅት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሊዝ የተረከበውን 5ሺ ካሬ ሜትር ቦታ በደላሎች አማካኝነት ሊሸጥ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።
GTNA መሬቱን ከተረከበ ሶስት አመት እንዳለፈው የጠቆሙት ምንጮቻችን ከጋንዲ ሆስፒታል ተቀንሶ የተሰጠው ቦታ ታጥሮ ለመኪና ፓርኪንግ አገልግሎት ብቻ እየዋለ ቆይቶ የመሠረት ሚድያ ሪፖርት በወጣበት ምሽት ዘገባውን ለማስተባበል በሚመስል መልኩ ጋዜጠኛው በምሽት የሚንቀሳቀሱ ሲኖ ትራክ መኪናዎች በማህበራዊ ሚድያ ገፁ መለጠፉ ይታወሳል።
-መሠረት ሚድያ-




