የጤና ባለሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያ በአዲሱ የደሞዝ ስኬል መሰረት እንዲከፈል ጠየቁ
(መሠረት ሚድያ)- ከወራት በፊት ጥያቄዎቻቸውን ይዘው ወደፊት በመምጣት ከፍተኛ ትኩረት አግኝተው የነበሩት የጤና ባለሙያዎች አልተፈቱም ያሏቸውን ጉዳዮች ይዘው ማሰማት ጀምረዋል።
የጤና ባለሙያዎቹ አሁን እያነሷቸው ያሉት ጥያቄዎች አዲሱ የደሞዝ ስኬል በሁሉም የጤና ተቋማት እና ክልሎች በአስቸኳይ እንዲተገበር እንዲሁም የጤና ባለሞያ ደሞዝ በተለየ መልኩ ታይቶ በድጋሚ እንዲሻሻል የሚል ይገኝበታል።
በተጨማሪም አዲሱ የትርፍ ሰዓት ክፍያ (Duty Payment) በአዲሱ የደሞዝ ስኬል እና መመሪያ መሰረት ከመስከረም 1 ጀምሮ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በአስቸኳይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኙ ባለሞያዎች መክፈል እንዲጀመር እና በቀደመው ታስቦ የተከፈላቸው ቀሪው ታስቦ እንዲከፈላቸው ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛሉ።
"የጥቅማ ጥቅም ማለትም የቤት፣ የተጋላጭነት፣ የሙያ፣ የበረሃ አበል፣ የትራንስፖርት ክፍያ ማሻሻያ በአስቸኳይ እንዲደረግ እንፈልጋለን" ያሉት የጤና ባለሙያዎቹ ጥሪያቸውን በጤና ሚኒስቴር የማህበራዊ ሚድያ ገፆች ላይ ለማስፈር ቢፈልጉም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአስተያየት መስጫ ሳጥኑን እየቆለፈ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
እስካሁን እንደ አብርሀ ጅራ ሆስፒታል ያሉ ጥቂት ሆስፒታሎች በአዲሱ የትርፍ ሰዓት ክፍያ (duty payment) ስሌት ለመክፈል ማስታወቂያ ማውጣታቸው ቢታወቅም በርካቶቹ ግን በድሮው ስሌት ላይ እንደሚገኙ ታውቋል።
የካቲት 12 ሆስፒታል በአዲሱ ደሞዝ ዱዩቲ አልከፍልም በማለቱ ከጤና ሚኒስቴር ደብዳቤ እንደተፃፈለት ታውቋል።
"ጤና ሚኒስትር ደብዳቤ ማንጋጋት ብቻ ሳይሆንተግባራዊነቱን ታች ወርዶ መከታተል የግዴታ ተልዕኮው ነው። የክልል ጤና ቢሮዎችና የዞን ጤና መምሪያዎች ሀላፊዎች መፈተሽ አለባቸው፣ ባለሙያ በመንግሥት እንድማረር እያደረጉ ናቸዉ" የሚሉት የጤና ባለሙያዎቹ ናቸው።
"በአዋጅ የጸደቀን የዱቲ ክፍያ መመሪያ ተግባራዊ አላደርግም የሚል አመራር ወይ የመንግስት ንቀት አለበት አልያም ጭር ሲል አልወድም ነው። ይህ ካልሆነ በስተቀር ደመወዝ ተሻሽሎ ከመመሪያ ውጭ ዱቲ በአሮጌው ደመወዝ የሚከፈልበት ምንም ምክንያት አይኖርም" በማለት ድምፃቸውን እያሰሙ መሆናቸውን ተመልክተናል።
-መሠረት ሚድያ-




