መናጆ ወይስ 'ጽምዶ'?! "የህወሃት አንዱ አንጃ አሁናዊ ከሻዕብያ ጋር ላድርገው የሚለው ቅንጅት መነሻው ከንቱ መዳረሻውም ከንቱ ነው"
በአቶ አበበ ገብረህይወት ተፅፎ በመሠረት ሚድያ እንዲታተም ፈቃድ ያገኘ
(መሠረት ሚድያ)- ህብረት መነሻ እና መዳረሻ አለው። ከአንድ ሁለት ይሻላል የምንልበት የአላማ እና የውጤት አንድነትን ይጠይቃል፣ (strategic alliance) የሚባለው መሆኑ ነው።
በጤናማ ህብረት ወይም መቀናጆ የህብረት አካላት ያላቸውን የቴክኒክ፣ ፋይናንስ፣ ዲፕሎማሲ ወዘተ አቅም ይዘው ይገናኛሉ። የዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው የሚቀናጁት አካላት የራሳቸው የተለየ አቅም ያላቸውን ያህል ሌላው መቀናጆ ያለው አቅም ወይም ችሎታ አይኖራቸውም። በቅንጅቱ ግን የዳበረ አቅም የመፍጠር እድል አለው።
የዚህ አይነት ቅንጅት ዳሩን መሃል የማምጣት እና ተገቢ ክብር የሚያሰጥ ህብረት ወይም መቀናጆ (Consortia or Partnership) ሊፈጥር ይችላል። ይህ መቀናጆ መነሻው እና መዳረሻው ላይ የአላማ፣ የሂደት እና ውጤት ግልጽነት እና አንድነት ስለሚኖረው የተሳካ ዘላቂነት ያለው የመሆን እድሉ ሰፊ ነው።
በአንጻሩ "የመናጆ" አይነት ቅንጅት ደግሞ አለ። መነሻ እና መዳረሻው ማካሄድ ወይም ማሻሻጥ ብቻ የሆነ። መናጆ ማለት ልትሸጠው ያሰብከውን በሬ ወይም እንስሳ ከሌላ የማትሸጠው ነገር ግን ገበያ አብረህ ይዘሀው የምትሄደው በሬ፣ ከብት ማለት ነው።
የመናጆ ስራ ማሻሻጥ ሊባል ይቾላል። ይህ ሁኔታ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች በየጊዜው ልናየው እንችላለን።
የህወሃት አንዱ አንጃ (faction) አሁናዊ ከሻዕብያ ጋር ላድርገው የሚለው ቅንጅት መነሻው ከንቱ መዳረሻውም ከንቱ ነው። የአለማ እና የውጤት አንድነት የሌለው።
መሰረቱ ህገወጥ የሆነ፣ ሉአላዊነትን የሚንድ መዳረሻው ሊሳካ የማይችለውን ሃገርን ለመበጥበጥ ብሎም ለማፍረስ የሚደረግ የመናጆ ትርኢት ነው።
የእንዲሸጥ የታሰበው የሻዕብያ ወጥነት ያለው "ኢትዮጵያን የማዳከም" ሸቀጥ አካል ነው። "ጽምዶ ሳይሆን መናጆ በሉት በስሙ።
*አቶ አበበ ገብረህይወት የትግራይ ግዜያዊ አስተዳደር ምክትል ሀላፊ በመሆን አገልግለዋል።
መረጃን ከመሠረት!



