ዛሬ አነጋጉ ላይ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ በሚገኘው መሪ 40/60 የጋራ መኖርያ ቤት ውስጥ ሽጉጥ በመጠቀም የተፈፀመው አስነዋሪ የወንጀል ድርጊት
(መሠረት ሚድያ)- አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ድሮ እምብዛም የማይታወቀው በመሳርያ የተደገፈ የወንጀል ድርጊት አፈፃፀም አሁን አሁን እየተስፋፋ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።
አብዛኛዎቹ በመሳርያ የታገዙ ወንጀሎች የዝርፊያ ተግባራት ቢሆኑም ዛሬ ከወደ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የተሰማው ግን ሴት አስገድዶ የመድፈር ፀያፍ የወንጀል ድርጊት ነው።
ዛሬ አነጋጉ ላይ 11 ሰዓት ገደማ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ውስጥ በሚገኘው መሪ 40/60 ኮንደሚኒየም የታች ወለል (ground) ክፍል መሳርያ ይዞ የነበረ ግለሰብ አንዲት ሴትን አስገድዶ መድፈሩ ታውቋል።
በስፍራው ያሉ ነዋሪዎች ለሚድያችን እንደጠቆሙት ግለሰቡ አነጋጉ 11 ሰአት ላይ ሽጉጥ በመያዝ እና የጋራ መኖርያ ቤቱን ጥበቃ በመደብደብ ውስጥ በመግባት ወንጀሉን ፈፅሟል።
"ሽጉጥ የያዘው ሰው ሴት ልጅ ደፍሮ ሄዷል፣ ጥበቃውን ደብድቦ ቢጮህም በፍጥነት የደረሰ የህግ አስከባሪ አካል አልነበረም" ያሉት ነዋሪዎቹ 'መጭው ጊዜ የበለጠ ያስፈራል' በማለት ስጋታቸውን ገልፀዋል።
ፎቶ: ድርጊት ፈፃሚው (በስተግራ)፣ የፀጥታ ባለሙያው (በስተቀኝ) እና ወንጀል የተፈፀመበት ቦታ
ወንጀሉ የተፈፀመበት ቤት የንግድ ቤት መሆኑ የታወቀ ሲሆን ምግብና መጠጥ ቤት የሚሰራ እና ብዙ ግዜ ቢበዛ እስከ ምሽቱ 6 ስዓት የሚሰራ መሆኑ ታውቋል።
"ወንጀለኛው መስታወቱን ሰብሮ ነው የገባው" ያሉት የአይን እማኞች ከበርካታ ደቂቃዎች በኋላ አንድ ሲቪል የለበስ የፀጥታ ባለሙያና በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ትብብር ቀጥሎ ባሉት ሌሎች ብሎኮች (ህንፃዎች ) ውስጥ ወንጀለኛው ተደብቆ መያዙ ታውቋል።
ይህ የመሠረት ሚድያ ዘገባ እስከወጣበት ሰዓት ድረስ የፀጥታ አካላት ከጣብያ ባለመምጣታቸው መኪና ተፈልጎ ወደ ፖሊስ ጣብያ እንደተወሰደ ታውቋል።
በዚህ ዜና ላይ የተካተተው ፎቶ ድርጊት ፈፃሚው፣ የፀጥታ ባለሙያው እና ወንጀል የተፈፀመበትን ቦታ ያሳያል።
-መሠረት ሚድያ-



