በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ውስጥ ዛሬ በንፁሀን ዜጎች ላይ በተፈፀመ ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸው ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በተደጋጋሚ በንፁሀን ዜጎች ላይ የሚፈፀምን ጥቃት ሲያስተናግድ የቆየው የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቡለን ወረዳ ዛሬም ከፍተኛ የሰላማዊ ዜጎች እልቂትን እንዳስተናገደ ሚድያችን ከስፍራው እየደረሱት ያሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
በዞኑ በኩጂ ቀበሌ ውስጥ ታጣዊዎች ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት በፈፀሙት ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን እና በርካቶች በሽሽት በየጫካው ስር ቤተሰቦቻቸውን ይዘው እንደገቡ ታውቋል።
"በማያውቁት የፖለቲካ ቁማር በተለምዶ 'ሸኔ' የሚባሉ ነገር ግን እዚያ አካባቢ ራሳቸውን አደራጅተው ከዋናው ሸኔ ጋር ግንኙነት ይኑራቸው አይኑራቸው በማይታወቁ የታጠቁ ሀይሎች ንፁሁን ዜጎች ተጨፍጭፈዋል" ብለው ቃላቸውን ለሚድያችን የሰጡት አንድ የአካባቢው ነዋሪ ናቸው።
"ለመንግስት ሀይሎች ጩኸት ብናሰማም እየሰሙ ያልሰሙ ሆነዋል። አንድም ሚድያ ስለሞታችን አልዘገበም፤ ድምጽ ሁኑን" ብለው ጥሪ አስተላልፈዋል።
በኩጂ ተብሎ በሚጠራው በዚህ ቀበሌ በ2013 ዓ.ም 298 ሰው በጉሙዝ ታጣቂዎች የተገደሉበት እና በጅምላ የተቀበሩበት ቀበሌ መሆኑ ይታወሳል።
በአሁኑ ጥቃት ከአንድ ቤተሰብ ስድስት አባላት የተገደሉባቸው እንዳለ የታወቀ ሲሆን በአካባቢው በአብዛኛው የሺናሻ ብሄር አባላት የሚኖሩበት ነው፣ ከሟቾቹ መሀል አብዛኛዎቹም የብሄሩ ተወላጅ መሆናቸው ታውቋል።
"አሁን ሟቾቹን እየቀበሩ ነው፣ ደውለው የነገሩኝ ነው። የጉሙዝ ልጆች ስደት ላይ ናቸው" በማለት አንድ የጉሙዝ ብሄር ተወካይ ስሜ አይጠቀስ ብለው ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት እንዲሁም የፌደራል መንግስት እስካሁን በግድያው ዙርያ ያሉት ነገር ባይኖርም የቡለን ወረዳ ወጣቶች ስፖርት ፅህፈት ቤት "ትኩረት ለባኩጂ ቀበሌ ነዋሪዎች፣ የሸኔ ታጣቂዎች ቶክስ በመክፈትና ቤት በማቃጠል ላይ ይገኛሉ፣ የፀጥታ ሀይሎች እንዲደርሱላቸው ጥሪ አስተላልፈዋል" በማለት በፌስቡክ ገፁ አጋርቷል።
በዚህ ዙርያ የክልሉን ፕሬዝደንት አቶ አሻድሊ ሀሰንን እንዲሁም የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊውን አቶ መለሰ በየነን በስልክ ለማግኘት ያረግነው ሙከራ ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካም።
-መሠረት ሚድያ-





